ቀጥታ፡

ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን አጋርነትና ፍቅር ለመግለጽ ለበአሉ 84 የእርድ እንስሳት በድጋፍ አበረከተ

ጎንደር ጳጉሜ 6 /2015  (ኢዜአ ) የጎንደር ከተማና የማእከላዊ ጎንደር ዞን ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን አጋርነትና ፍቅር ለመግለጽ በ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የገዛቸውን 84 የእርድ እንስሳት ለበአል መዋያ በድጋፍ አበረከተ ፡፡

የጎንደር ከተማን ህዝብ የወከሉት አቶ አድማስ ደሞዜ በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የከተማው ህዝብ  ሰራዊቱ በአሉን በደስታ እንዲያሳልፍ 36 የእርድ እንስሳት በዛሬው እለት አስረክቧል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት ከህዝብ አብራክ የወጣ ለህዝብ ሰላምና ደህነንት ህይወቱን የሚሰዋ በመሆኑ ህዝቡ ለሰራዊቱ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽ ድጋፉን ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

"ድጋፉ የህዝቡና የመከላከያ ሰራዊቱ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው " ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው።፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አላምረው ከበደ በበኩላቸው፤ የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ የበአል መዋያ የገዛቸውን 48 የእርድ እንስሳት ህዝቡን በመወከል ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡


 

''ህዝቡ ለበዓል መዋያ ለሰራዊቱ ያደረገው የእርድ እንስሳት ድጋፍ የሰራዊቱን ህዝባዊነትና ተቀባይነት የሚያጎላ ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጄኔራል ማርዬ በየነ ናቸው፡፡ 

የከተማው ህዝብ በህግ ማስከበር ስራው ለሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ አዲሱ አመት የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም