ቀጥታ፡

በቀጣዩ ዓመት ፈተናዎቻችን እጅግ ቀንሰው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ከአልማዝ ጠንክሮ፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በጽኑ መሠረት ላይ እናጸናዋለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፦ በቀጣዩ ዓመት ፈተናዎቻችን እጅግ ቀንሰው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ከአልማዝ ጠንክሮ፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በጽኑ መሠረት ላይ እናጸናዋለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለ2016 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም በፈጣሪ ቸርነት 2015ን አልፈን ወደ አዲሱ ዘመን ደርሰናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በውጣ ውረድ ውስጥ እያሸነፈች ተጉዛለች ሲሉም አክለዋል።

ጽኑ መርሕ፣ ብርቱ ሕዝብና የማይሸነፍ አምላክ ስላለን እዚህ ደርሰናል ሲሉም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ብዙ ነገሮችን አሳክተናል፤ አያሌ ፈተናዎችን በድል ተወጥተናል፤ እልፍ መሰናክሎች ቢደረደሩም ጠንካራ መሰረት ሆነውን አልፈዋል ብለዋል።

የተሳኩልን ሁሉ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ውጤቶች ናቸው፤ የተፈተንባቸው ደግሞ በመለያየት የተነሣ የመጡ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

በቀጣዩ ዓመት ፈተናዎቻችን እጅግ ቀንሰው፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ከአልማዝ ጠንክሮ፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በጽኑ መሠረት ላይ እናጸናዋለን ሲሉም ተናግረዋል።

ልማትና ብልጽግናዋን ወደሚመጥናት ደረጃ እናሻግረዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ብልጽግና ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም