በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሠላምና ልማት በጋራ መሥራት ይገባል - የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሠላምና ልማት በጋራ መሥራት ይገባል - የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ፣ ዻጉሜን 6/2015 (ኢዜአ)- በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሠላምና ልማት እንዲሁም አንድነት እንዲጠናከር በጋራ መሥራት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ አሮጌውን ዓመት አሰናብታ አዲሱን የመቀበል ዋዜማ ላይ ትገኛለች።
የ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ መልካም ተግባራት የተከናወኑበት ዓመት መሆኑን የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እነዚህንም መልካም ተግባራት በመጪው የ2016 ዓ.ም ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
እንዲያም ሆኖ የ2015 ዓ.ም አገሪቱ ፈተናዎች እንዳጋጠሟት ጠቁመው በአዲሱ ዓመት እነዚህ ችግሮች የሚወገዱበት ዓመት እንዲሆን መሥራት ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሠላምና ልማት መረጋገጥ እንዲሁም አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ ዓመት እንዲሆን ይመኛል ብለዋል።