የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛ እና የመጨረሻ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ የሚቀይር ነው- ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛ እና የመጨረሻ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ የሚቀይር ነው- ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ)፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛ እና የመጨረሻ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ የሚቀይር መሆኑን የዘንድሮ በጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ገለጹ፡፡
ትናንት በተካሄደው 11ኛው የበጎ ሰው ሽልማት በትምህርት ሚኒስትርነት ሀገራቸውን ያገለገሉት ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው መንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ብትሆንም ዓባይን ጨምሮ ወንዞቿን በተገቢው መልኩ እንዳልተጠቀመች አስታውሰዋል፡፡
ይህም ያላትን ሃብት በመጠቀም እንዳትለማ አድርጓት መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛው እና የመጨረሻው ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ የሚቀይርና መልከ ብዙ ፈተናዎችን ለማለፍ የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ብዙ ችግር ያሳለፈች ሀገር መሆኗን የተናገሩት ዶክተር ያየህይራድ፣ ኢትዮጵያን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ዘመኑን የዋጀ መፍትሔ በማፍለቅ መፍታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡