ቀጥታ፡

መጪውን አዲስ ዓመት ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ)፡- መጪውን አዲስ ዓመት ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን  እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

የሃይማኖት አባቶቹ መጪውን አዲስ ዓመት አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ፤ አዲሱ ዓመት  የእርቅ፣ የይቅርታና የሰላም እንዲሆን ተመኝተዋል።

አዲሱ ዓመት ስናከብር የተቸገሩን ከመርዳት ባለፈ እርስ በእርስ በመዋደድና አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡


 

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅርና የበረከት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ምዕመናን አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻቸውን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አዲሱ ዓመት የታመሙ የሚድኑበት የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ምዕመናን ለእርቅና ለውይይት ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አዲሱ ዘመን ኢትዮጵያዊያን በመቻቻልና በመዋደድ የፈጣሪያቸውን በረከት የሚያገኙበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ፣ ለመላው ኢትዮጵያን እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያናት መካነየሱስ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮናስ ይገዙ አዲሱ አመት የይቅርታ የአንድነትና ወደ ሰላም የመመለስ ጊዜ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ በአዲሱ ዓመት  የጥላቻ ትርከቶች በበጎ ትርክቶች እንዲተኩ ጥረት እናድርግ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም