የሕዳሴው ግድብ ኢትዮዽያዊያን ከተባበርን ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መፈጸም እንደምንችል ለዓለም የምናሳይበት ነው---የሐረር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ ኢትዮዽያዊያን ከተባበርን ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መፈጸም እንደምንችል ለዓለም የምናሳይበት ነው---የሐረር ከተማ ነዋሪዎች
ሐረር፣ ዻጉሜን 6/2015 (ኢዜአ)-የሕዳሴው ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮዽያዊያን ከተባበርን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መፈጸም እንደምንችል ለዓለም የምናሳይበት ነው ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክቶ ኢዜአ የተለያዩ የሐረር ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ሻንበል አባተ ደምሳሽ እንደገለጹት፣ የሕዳሴው ግድብ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት ነው።
እንደ ሀገር የገጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም የሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራን በድል ለማጠናቀቅ መቻሉ የተለየ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ግድቡ የደረሰበት ደረጃ በህብረት ከሰራን በራስ አቅም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጭምር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ በመሆኑ ለሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የምናደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ እና የመጨረሻ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቅን ስሰማ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ያሉት ደግሞ አቶ ገመዶ ሃይሉ የተባሉ የሐረር ከተማ ነዋሪ ናቸው።
በህዳሴው ግድብ "እኛ ኢትዮጵያዊያን ተባብረን ከሰራን የማናሳካው የልማት ፕሮጀክት እንደማይኖር ለዓለም ህዝብ አሳይተናል" ሲሉም አክለዋል።
በራስ ጉልበትና አቅም መስራት እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፣ የግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለሌሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ለማድረግ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ከዲር አብደላ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የኢትዮዽያን ልማት ለማፋጠን የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ የውሃ ሙሌት ስራው መጠናቀቅ የመንግስትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ማሳያ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ስኬታማ እንዲሆን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ከዲር ገልጽዋል።
የግድቡ አራተኛ ዙርና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅን መስማት ለኢትዮጵያውያን ደስታና ብርታት ይሰጣል ያሉት ደግሞ መምህር በፍቃዱ ታደሰ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት ለግድቡ ግንባታ ባደረጉት ድጋፍ ለስኬት መብቃቱን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ "በተለይ ለአገር በጋራ መቆም ለስኬት እንደሚያበቃ ግድቡ ጥሩ ማሳያና ማስተማሪያ ነው" ብለዋል።
"የሌሎች ድጋፍ ሳይኖር ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ርብርብ የተገነባው የሕዳሴው ግድብ የአይቻልም መንፈስ የተሰበረበትና ትውልዱ በታሪክ የሚዘከርበት በመሆኑ በቀጣይም ድጋፋችንን እናጠናክራለን" ብለዋል።