የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት ነው - ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት ነው - ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ)፡- የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት አብስረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን በማስመልከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስና ጂኦ ፖለቲካ ተመራማሪ እንዲሁም የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖን አነጋገሯል።
ዶክተር ያዕቆብ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይጀመር በርካታ ጫናዎች ሲደረጉ እንደነበር በማንሳት፤ ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ በኋላም የነበሩ ፈተናዎችን ኢትዮጵያ በጽናት ማለፏን ተናግረዋል።
የግድቡ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት መጠናቀቅ የነበረውን ጫና ሙሉ በሙሉ የቀለበሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበር በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ በያዘችው እቅድ መሰረት የግድቡን ውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባበታለች ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከግል ጥቅም ይልቅ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም እና ለቀጣዩ ትውልድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያነሱት ዶክተር ያዕቆብ ይህንንም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን ተቋቁመው በጥሪታቸው እየገነቡት ያለው ይህ ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ግድብ አሁን ፍሬው መታየት ጀምሯል ብለዋል።
የግድቡ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅም የህዝቡ የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የእውቀት አስተዋጽኦና የጸሎት ትጋት ውጤት መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የውሃ ሃብቶቿን ለማልማት ስታቅድ ጎረቤት ሀገራትን እና የታችኛው ተፋሰስን የጋራ ልማት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትም በቂ ውሃ ወደታችኛው ተፋሰስ አገራት እንዲያለፍ በማድረግ መከናወኑን አንስተዋል።
አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌትም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በቂ የውሃ መጠን እንዲያልፍ በማድረግ መከናወኑን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ወንዞቿ ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸው ለጎረቤት ሀገራትም ትልቅ ጸጋ ነው ያሉት ዶክተር ያዕቆብ ሆኖም አንዳንድ ሀገራት ሉዓላዊ መብቷን ለመገደብ ሲሞክሩ ይስተዋላል ብለዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብት እንዳላት በሚገባ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነትና በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የመጠቀም መርህን ይዛ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አረጋገጠዋል።
በቀጣይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና የወደፊቱን ትውልድ የልማት መብት የሚያስከብር ስምምነት እንዲኖር በጥንቃቄ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።