የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፡-የሃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌዎች የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህል፣ የእምነትና የቋንቋ ብዝሀነት ኅብረ ብሔራዊት ሀገርን በመፍጠር የሕዝቦቿ የአንድነት ማስተሳሰሪያ ሀገራዊ እሴት ሆኗል።
ይህም ኢትዮጵያውያን ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በአንድነትና በአብሮነት ታግለው የሀገራቸውን ነጻነትና ሕልውና ማቆየት አስችሏል።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የሕዝቦች አብሮነትና ትብብር ኢትዮጵያን በጋራ ያቆመ ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል።
መላዕከ ፀሐይ አባ ወልደገብርኤል በበኩላቸው ወጣቶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእኩልነት እና በመከባበር ላይ ለመገንባት የሚደረገውን ርብርብ በቅንነት ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን በምግባር በማነጽ በኩል የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ በመግለጽ፤ እርሳቸውም የበኩላቸውምን ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ያነሱት።
የጋሞ የአገር ሽማግሌ ሳድቃ ሳሜ እንደሚሉት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ችግሮችን በሰከነ መንፈስ ማለፍ ይገባል።
ከሚያለያዩ ሀሳቦች ይልቅ የሚያቀራርቡ ላይ ትኩረት በማድረግ ለአገር ግንባታ በጋራ መትጋት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
አቶ ለማ ዴሬሳ የአገር ፍቅር መገለጫዎች ብዙ መሆናቸውን በማንሳት፤ ተተኪው ትውልድ ለአገር ልማትና ዕድገት አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን ማፍለቅ እንደሚገባው ተናግረዋል።
አረጋውያን ያለፉበትን የሕይወት ውጣ ውረድ ለተተኪው ትውልድ የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
ጠንካራ አገር ለመገንባት ተተኪው ትውልድ ከሁሉ በላይ ችግሮችን በመነጋገር፣ በመመካከርና በሀሳብ የበላይነት የማመን ልምድን ሊያዳብር እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን "በሕብር የተሰራች አገር" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች በመከበር ላይ ይገኛል።