ቀጥታ፡

አብሮነት የትናንት ማንነታችን፣ የዛሬ ኅልውናችን፣ የነገ ዕጣፈንታችን ነው-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፡- አብሮነት የትናንት ማንነታችን፣ የዛሬ ኅልውናችን፣ የነገ ዕጣፈንታችን ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በህብር የተሰራች ሀገር በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ያለውን የአብሮነት ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፏል።

ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ይቀርባል ፦

አብሮነት የትናንት ማንነታችን፣ የዛሬ ኅልውናችን፣ የነገ ዕጣፈንታችን ነው!

ስለአብሮነት አዘውትሮ መናገር የሚያስፈልገው ለኅልውናችን መቀጠል ዋስትና ስለሚሰጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ስንል ኅብረት ፈጥሮ ሀገራችንን ከማንኛውም ስጋት በመጠበቅና በማበልጸግ በኹሉም መስክ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና በፈታኝ ወቅቶችም በጋራ በመቆም ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ነው፡፡

አብሮነት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያፀና፣ ብዝኃነታችንን የጥንካሬያችን ምንጭ የሚያደርግ፣ አንዳችን ለሌላችን በማሰብ ከብረት የጠነከረ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥር ዕሳቤ እንዲሁም ተግባር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በደም፣ በኢኮኖሚ፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በሥነ ልቦና፣ በባህል እና በሌሎችም ማኅበራዊ እሴቶች የተጋመደ የአንድ ታላቅ ሀገር ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የትናንት ማንነቱ፣ የዛሬ ኅልውናው እና የወደፊት ዕጣፈንታው የተሳሰረ በመኾኑ የባህላችን እሴት፣ የአይበገሬነታችን ምንጭ የኾነው አብሮነቱን አጥብቆ መቀጠል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ መከፋፈልና መለያየት እንደ ሕዝብና ሀገር ከማሳነስ በስተቀር የሚያመጣልን ትርፍና ድል የለውም፡፡

የኢትዮጵያውያን ኅብር ሀገር ገንብቷል፤ ሕዝቦቿን በአብሮነት ከማንኛውም ባዕድ ወራሪ ለመጠበቅ እና በራሳችን ነፃነት መወሰን እንደምንችል በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አሳይተናል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድነቷ ታፍራ እና ተከብራ እንድትቆይ አባቶቻችን መሥዋዕትነት ሲከፍሉ አብሮነት ለሀገር ኅልውና ያለውን ዋጋ በመመዘን ነው፡፡

ዐዲሱ ትውልድም በሀገሩ አንድነት እና በሕዝቦች አብሮነት ላይ በውስጥ ባንዳዎችም ኾነ በውጭ ጠላቶች የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ጥቃትና እና የሚዘረጉ የሴራ ገመዶችን በመረዳት ልክ እንዳባቶቹ ለአብሮነት ቀናዒ መኾን አለበት፡፡ አንድነታችንን ለመድፈር እና አብሮነታችንን በፅንፈኝነት አስተሳሰብ ሊሸረሽሩ የሚፈልጉ አካላትን ጆሮ በመንፈግ ልናወግዛቸው ይገባል፡፡

አንድነታችንን በመናድ ሊያዳክሙን የሚፍጨረጨሩ ፅንፈኞችን ተባብረን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን በማክሰም የሀገራችንን ደኅንነትና የሕዝቦቿን ሰላም ማረጋገጥ ከኹሉም ይጠበቃል፡፡ አብሮነት የማይጥማቸው ፅንፈኞች ብሔርን ከብሔር፤ ሃይማቶትን ከሃይማኖት በማጋጨት የቆየ አብሮነታችንን ለመናድ ብዙ ርቀት ቢጓዙም መቼም ቢኾን እንደማይሳካለቸው ልናሳያቸው ይገባል፡፡

ዛሬ የአብሮነት ቀንን ስናከብር ሀገራችን ኢትዮጵያ በኅብር የተገነባችና በጋራ መሥዋዕትነት ተጠብቃ የቆየች መኾኗን ወደ ኋላ መለስ ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ዕጣ ፈንታችን በእጅጉ የተሳሰረ መኾኑን ይበልጥ በመገንዘብ አብሮነታችንን የሚፈታተኑ ተግባራትና አስተሳሰቦችን ለመታገል ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት ዕለት መኾን ይኖርበታል፡፡

መልካም የአብሮነት ቀን ይሁንልን!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም