ቀጥታ፡

አዲሱ ትውልድ አገርን በመገንባት ሂደት የሚኖረውን ተሳትፎ ለማጠናከር የመደመርን እሳቤ አንግቦ  ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል-አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ

ድሬዳዋ፤ ጳጉሜን 5/2015 (ኢዜአ) ፡-አዲሱ ትውልድ አገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ እያበረከተ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የመደመርን እሳቤ አንግቦ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ አስገነዘቡ፡፡

"ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር" በሚል መሪ ሃሳብ የትውልድ ቀን በድሬዳዋ የአዲሱን ትውልድ ሚና በሚያስገነዝብ የፓናል ውይይት ተከብሯል።

በውይይቱ ላይም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንደገለፁት፤  በትውልዶች ቅብብሎሽ የተረከብናትን አገር በተሻለ ቁመናና ከፍታ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አዲሱ ትውልድ በአገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ እና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል ።

እንደ ድሬደዋም ሆነ እንደ አገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በውጤት ለመደምደም አዲሱ ትውልድ የጠራ ራዕይ በማንገብ እና በመደመር እሳቤ በመጓዝ የተሻለች አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ኃላፊነቱን በትጋት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል ።

ይህንን መሠረታዊ አላማ ከዳር ለማድረስና በአዲሱ አመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትውልድ ቀን የተካሄደው ውይይት መሠረታዊ ግንዛቤን አስጨብጧል ብለዋል።

የፓናል ውይይቱን ያዘጋጀው የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊራኦል ቡልቻ በበኩላቸው፤  የመጪው ጊዜን የኢትዮጵያ ብስራት ለማወጅ እና ከፍታዋን ለማረጋገጥ የትውልድ የተጋመደ እና የተደመረ ርብርብ ወሳኝ ሚና አለው።

እንደ አገር የጀመሩትን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞዎች ዳር ለማድረስም የዛሬው ታሪካዊ ቀን የራሱ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል።

በትውልድ ቀን የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት ወጣቶች በአዲሱ አመት በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር እንደሚገባቸው አስታውቀዋል ።

የድሬዳዋ የህፃናት ምክር ቤት አባል የሆነችው ተማሪ ሜሮን ታምራት፤ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ተከብሮ የተሻለች አገር እንትሆን በማድረግ ውስጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቤተሰብ ለአዲሱ ትውልድ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት ብላለች።

መሰል ከወጣቶች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች አገር ተረካቢ ትውልድ በአገሩ ጉዳይ የሚጠበቅበትን ታላቅ ኃላፊነት ለመረዳት ያግዛል ያለችው ደግሞ ወጣት ባህር ውብሼት ናት።

ወጣቷ እንዳለችው፤ በአገር ግንባታ ላይ ሁሉም የበለጠ መስራት ይጠበቅበታል ።

ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የትውልድ ቀን የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶችና ሴቶች በተሳተፉበት ተከብሮ ውሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም