የህዳሴው ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለትውልድ የሚሸጋገር አሻራ ማስቀመጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው - ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለትውልድ የሚሸጋገር አሻራ ማስቀመጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ አብስረዋል።

የዛሬው ትውልድ የታሪክ ማስታወሻ የነገው ትውልድ ገጸበረከት የሆነው የህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት "የትውልድ ቀን" ኢትዮጵያ የብዙ ትውልዶች ድምር በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ባለበት ወቅት ነው የተበሰረው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንደሚሉት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስ የጋራ ጥረት ውጤት ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ዮናስ አሽኔ ዓባይ የኢትዮጵያ ማንነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የዛሬው ትውልድ አሻራ የነገው ትውልድ ገጸበረከት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ገልጸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከዓባይ ጋር ያላትን ትስስር የሚያጸና መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርኃነመስቀል ጠና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚነጋገሩበት የጋራ ቋንቋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ 4ኛ ዙር ሙሌት ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥም ሆና ማንኛውንም ፕሮጀክት ማሳካት እንደምትችል በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድህነትን በማሸነፍ ለመጭው ትውልድ ብልጽግናን የምናወርስበት የአንድነታችን አርማ፤ የማሸነፋችን ምልክት ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመን በዚህ ልክ መለወጥ ከቻልን ሰላማችንን በጋራ ብናረጋግጥ የት እንደርስ ነበር የሚለውን መላው ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያየው ይገባል ነው ያሉት።

ትናንት ያጋጠሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግረን እዚህ ደርሰናል፤ የዛሬ ፈተናዎችንም አልፈን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እንደምናደርግ ያለፍንበት መንገድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከልመና የምንወጣበት ድህነትን የምናሸንፍበት ፕሮጀክት በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ለግንባታው መጠናቀቅ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ዶክተር ዮናስ አሽኔ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ አገራትን የሚያስተሳስር በጋራ የመልማት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ የመጠቀም ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም