ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያቀደችውን እንደምታሳካ በህዳሴው ግድብ ላይ በተግባር አሳይታለች - የአሶሳ ነዋሪዎች

አሶሳ ፤ ጳጉሜን 5 /2015(ኢዜአ)፡ - ኢትዮጵያ ያቀደችውን ከማሳካት የሚያግዳት እንደሌለ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ  በተግባር  ማሳየቷን  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ  ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር  ዶክተር አቢይ አሕመድ  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን  በስፍራው ተገኝተው ይፋ ማድረጋቸውን  ቀደም ሲል ተገልጿል።

ይህን ተከትሎ ኢዜአ በአሶሳ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ፤ በቀጣይ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ሁሉ ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ ድጋፋቸውን አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኢብራሂም አዙቤር እንዳሉት ፤  በህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሂደት የተለያዩ ፈተዎችን አልፎ ስኬታማ በመሆኑ አስደሳች  ነው፡፡

አሁን ላይ  የፕሮጀክቱ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በሀገሬ ኮርቻለው  ያሉት  አቶ ኢብራሂም፣ የህዳሴው ግድብም ኢትዮጵያ ያቀደችውን ከማሳካት የሚያግዳት እንደሌለ ግድቡ በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ሃገራት የተፈጥሮ ሃብታቸውን በሚገባ አልምተው እንዲጠቀሙ የህዳሴው ግድብ ምሳሌ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ወጣት ዙዛና መኮንን በበኩሏ ፤ የህዳሴው ግድብ ለመላው ኢትዮጵያውያን የህልውናችን መሰረት ነው ብላለች፡፡


 

ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ የቱሪዝም ማዕከል በመሆን   በሚፈጠረው የስራ እድል በተለይም ወጣቱ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያላትን ተስፋ ወጣቷ ገልጻለች፡፡

አራተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ስትሰማ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብላለች፡፡

በራሳችን አቅም መልማት እንደሚቻል ግድባችን በተግባር አሳይቶናል ያሉት  ደግሞ አቶ እንቁ ወርቁ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡


 

በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት የእኛን መልማት የማይፈልጉ በፈጠሩት ጫና አልተንበረከክንም ያሉት አስተያየት ሰጪው ፤ ሌሎች ተጨማሪ ግድቦችን ለመገንባት መነሳት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ወጣት ሙሉአለም አስቻለው በበኩሉ ፤ በቀጣይ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ሁሉ ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ተግባራዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም