የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረትን አባል በማድረግ ተጠናቀቀ

704

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦በሕንድ አስተናጋጅነት ኒውዴልሂ ከተማ ውስጥ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የቡድን 20 አባል አገራት የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረትን 21ኛ አባል በማድረግ ዛሬ ተጠናቋል።

በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ዳ ሲልቫ የቡድን 20 ፕሬዝዳንትነት ቀጣይ መንበር አስረክበዋል።

ሉላ ዳ ሲልቫ ማኅበራዊ አካታችነትን፣ ረሃብን መዋጋት፣ የኃይል ሽግግርን እና ዘላቂ ልማትን የቡድን 20 አገራት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጧቸው እንደሆነም ከወዲሁ ይፋ አድርገዋል።

ጉባዔው 55 አባል አገራት ያቀፈውን የአፍሪካ ኅብረትን ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ የቡድን 20 አባል አድርጎ ተቀብሏል።

የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 ሃያ አንደኛ አባል ሆኖ መቀላቀሉ የቡድኑን አካታችነት መርህ እንደሚያጎላው የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

ሕንድ ባስተናገደችው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተከፋፈሉ የዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል ስምምነትን መፍጠር ችላለች ተብሏል።

ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ላቅ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንደሆነም ተገልጿል።


 

ጉባዔው የኒውዴልሂ የጋራ መግለጫ ሰነድ ይፋ በማድረግ ሲጠናቀቅ ሁሉም የቡድን 20 አባላት አገራት በዓለም ዙሪያ ሰላም፣ ደህንነት እና ግጭት በማስወገድ አንድ ሆነው ለመስራት ተስማምተዋል።

ሰነዱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ገቢራዊ ለማድረግ እኤአ እስከ 2030 ድረስ ከ5 ነጥብ 8 እስከ 5 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

እንዲሁም እስከ 2030 ድረስ ለታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች 4 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸውና ይህም እኤአ በ2050 የካርባን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ እንደሚረዳቸው ግልጽ አድርጓል።

በተጨማሪም አባል አገራት የኃይል እርምጃን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም