ቀጥታ፡

4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በርካታ ፈተናዎችን በጽናት አልፈው ያገኙት ብስራት ነው - የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል   

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015 (ኢዜአ)፦የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በርካታ ፈተናዎችን በጽናት አልፈው ያገኙት ብስራት መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ፡፡      

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ዛሬ አብስረዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው  በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በጸሎታቸው በሥራው ውስጥ የተሳተፋትን ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ  በማለት  መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡  

"የሕዳሴ ግድብን ውኃ ሞልተን ኢትዮጵያ አይበገሬና የምትፈልገውን ማሳካት የምትችል እንደሆነች እንዲታወቅ በማድረግ የትውልድን ልብ የሚያክሙ ሥራዎችን ጀምረናል" ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ 

ኢትዮጵያዊያን በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ያሳዩትን ትብብር በሌሎች የልማት ስራዎችም መድገም እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡   

የ4ተኛው ዙር ውሃ ሙሌት በሚመለከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል፤ የህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌት ስኬት በርካታ ፈተናዎች በጽናት ታልፈው የመጣ ብስራት ነው ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ እንዳይደርስ በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁሉንም በጽናት በማለፍ የግድቡ ሙሌት እንዲሳካ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡     

የሙሌቱ በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ለጋራ ዓላማ ከቆሙ የማይሻገሩት ፈተና እንደሌለ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

የህዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዕድገት ጉዞ ስኬት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበርክት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

ለኢትዮጵያ ልማት በጋራ መቆም እንደሚገባ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተመዘገበው ስኬት ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከልዩነት ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፍላጎት የትኛውንም አገር ሳትጎዳ በህዳሴ ግድቧ መልማትና ማደግ ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ወጣቱ ትውልድ ይህን ተገንዝቦ ለኢትዮጵያ የሚጠበቅበትን ማበርከት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡     

ኢትዮጵያዊያን በሕዳሴ ግድብ ያሳዩትን አንድነትና የዓላማ ጽናት በሌሎች የልማት ስራዎችም ሊደግሙት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም