ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ዕውን እንደሚሆን የማብሰሪያ ደውል እና የአዲስ ዓመት ብስራት ነው--ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ  ፣ጳግሜን5/2015 (ኢዜአ):- የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ስኬት የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ በተግባር ዕውን እንደሚሆን የማብሰሪያ ደውልና ለትውልዱም የአዲስ ዓመት ብስራት ነው ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

ግድቡ ልማትን በማፋጠን ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጉዞ ዳር ለማድረስ ወሳኝ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎችም የግድቡ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ የአገራችን መፃኢ ዘመን የተሳካ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የልብ ትርታ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በሁሉም ዘንድ ብስራትን ፈጥሯል።

ግድቡ እየተገነባ ባለበት ሥፍራ የሚገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ለኢዜአ በስልክ እንደገለጹት፤ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን የመደመርና የአብሮነት መገለጫ ነው።

የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተደምረው በአብሮነትና በጽናት ሰርተው ያመጡት ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል። 

አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ መንገድ መጠናቀቅ የሁሉንም ዜጋ መንፈስ ያለመለመ የአዲስ ዓመት ታላቅ ብስራት መሆኑንም ከንቲባው ተናግረዋል።

"በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድነታቸውን አጽንተው ከሰሩ ያሰቡትን ማሳካት እንደሚችሉ የሕዳሴው ግድብ ጥሩ ማሳያ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለጻ ግድቡ የአገራችንን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ፣ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥና ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጉዞ ዳር ለማድረስ ወሳኝ ነው።

የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለዘላቂ ልማት እና ሰላም መረጋገጥ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ድጋፍ በማጠናከር ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማውረስ ተግተው እንዲሰሩም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃ ሙሌቱን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የተበሰረው የውሃ ሙሌት ሥራ ለዜጎች ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

አቶ ኤሊያስ መሐመድ የተባሉ ነዋሪ " የግድቡ ሙሌትና የመንግስት ቁርጠኝነት ትልቅ ተስፋ አሳድሮብኛል" ብለዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዮሃና ታምራት በበኩሏ ዛሬ በተከበረው በጳጉሜን-5 የትውልድ ቀን የተሰማው የሕዳሴው ግድብ ዜና የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ያነቃቃ መሆኑን ተናግራለች።

"እኛ ከወላጆቻችን የምንጠብቀው ይህንን ደስታ ይበልጥ ከማሳደግ ባለፈ የተሻለ ሰላማዊና በዜጎች መካከል ፍቅር የሞላበት አገር እንዲያስረክቡን ነው" ብላለች።

የሕዳሴው ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን ዶክተር ዐቢይ በዛሬው እለት ማብሰራቸው የሚታወስ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም