የደብረ ማርቆስና አካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ማርቆስና አካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው
ደብረ ማርቆስ ፤ ጳጉሜን 5 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- የደብረ ማርቆስና አካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ጎጃምና የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጀነራል ሙሉ ሞገስ ገለጹ።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ከከተማ አስተዳደሩና ኮማንድ ፖስቱ ጋር ተወያይተዋል።
ብርጋዴል ጀነራል ሙሉ ሞገስ በዚሁ ጊዜ የደብረ ማርቆስና አካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበረሰቡን በማስተባበር በተደረገ ጥረትም አሁን ላይ የከተማውና አካባቢው ሰላም መጠበቁን ጠቅሰው፤ ለዚህም ማህበረሰቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅረበዋል።
በትብብር በተከናወነው ስራ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን አሁንም ጠንካራ ድጋፍና ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
''የሰላም ዋጋው ታላቅ ነው'' ያሉት ብርጋዴል ጀነራሉ ሰላም የሚረጋገጠው በፀጥታ ሃይሎች ጥረት ብቻ ሳይሆን በጋራ ተሳትፎ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስትዳደር ከንቲባና የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መንበሩ ዘውዴ በበኩላቸው ውይይቱ የከተማውንና የአካባቢውን ሰላም አስጠብቆ አብሮነትን ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።
በከተማው የተስተዋለው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ማህበረሰቡ ከዚህ ቀደም ካደረገው እገዛ በላይ የፀጥታ መዋቅሩን መደገፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የንግዱ ማህብረሰብና የመንግሥት ሰራተኞች ተሳትፈዋል።