ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬታማነት ፈተናዎችን በፅናት የምትሻገር ሀገር እየተፈጠረች መሆኑን አሳይቶናል..የምዕራብ ሀረርጌ ዞንና የጅማ ከተማ ነዋሪዎች

ጭሮ/ ጅማ፤ ጳጉሜ 5/2015(ኢዜአ)-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬታማነት ፈተናዎችን በፅናት የምትሻገር ሀገር እየተፈጠረች መሆኑን አሳይቶናል ሲሉ የምዕራብ ሀረርጌ ዞንና ጅማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

4ተኛውን ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ አስመልክቶ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች እንዳሉት ኢትዮጵያ ወደ ስኬት እያመራች መሆኑን ያሳየ ክስተት ነው።

በዞኑ የጭሮ ከተማ የሆቴል ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ወይንሸት ጌታሁን፣ የህዳሴ ግድብ በስኬት እዚህ መድረሱ የጋራ ውጤት እንደሆነና እጅግ የኮሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ከ120 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ለህዳሴው ግድብ ማድረጋቸውን አውስተው እንደ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሀገራችን ወደ ፊት በኢኮኖሚ እድገት ከፍ እንደምትል ያየንበት በመሆኑ በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የዞኑ ጉምቢ ቦርደዴ ነዋሪው አቶ አብዱማሊክ አህመድ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ተጀምሮ ዛሬ እስሚደርስ ድረስ ከወር ደሞዛቸው ቦንድ በመግዛት የግድቡን ግንባታ ሲደግፉ መቆየታውን ተናግረዋል።


 

ዛሬ ግድቡ በ4ተኛ ዙር ሙሌትን በመስማታቸውና የስኬቱ አካል በመሆናቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው በቀጣይም በሀገር ልማት ላይ ግንባር ቀደም ታሳታፊ እንዲሆኑ እንዳነሳሳቸው ገልፀዋል።

ሀገሪቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ እንዲህ አይነት ትልቅ የልማት ፕሮጀክት ማሳካቷ ሁሉንም ዜጋ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈሪድ ይስሃቅ፣ የዞኑን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ህዝብ ባደረገው ያልተቋረጠ ርብርብ የዛሬውን ውጤት ማየት መቻል እድለኝነት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ዞን አርሶ አደሩ፣ እናቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች በሚችሉት ሁሉ ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።


 

በምእራብ ሀረርጌ ዞን ለህዳሴው ግድብ ከቦንድ ግዢና የተለያዩ በአይነት ከ526 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድጉንም ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ሙሌት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬታማነት ፈተናዎችን በፅናት የምትሻገር ሀገር እየተፈጠረች መሆኑን ያሳየ ነው ሲል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንና  የግድቡን ስኬት በጉጉት የሚጠብቁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወጣት ያሲን መሀመድ፣ የግድቡ አራተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰቱን ገልጾ ''ለአመታት የደከምንበት ሀብታችን በመሆኑ በስኬቱ እንኮራለን'' ብሏል።

በህዳሴ ግድቡ በግሉ በርካታ አስተዎጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጾ ቦንድ በመግዛት፣ በማስተባበር እና በሌሎችም የተለያዩ ስራዎች ላይ የራሱን አሻራ ለማኖር ሲሰራ መቆየቱን ተናግሯል።

''የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መላው የሀገራችንን ህዝብ በአንድነት ለአንድ አላማ ያቆመ የሀገራችንን ልማት የሚያፋጥን በመሆኑ የተለየ ትኩረት አለኝ'' ብሏል።

የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት የብስራት ዜናን ስሰማ በእጅጉ ተደስቻለው'' ያለው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አወል ኢብራሂም ናቸው።

''በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት መላው የሀገሪቱ ህዝብ የተሳተፈበት ትልቅ የሀገር ሀብት በመሆኑ እኔም በግሌ በተለያየ መልኩ ተሳትፎ አድርጊያለው ''ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ኩራትና የህብረታችን ምልክት በመሆኑ ልንጠብቀው  ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም