የህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት አገራዊ አንድነትን የበለጠ የሚያጸና ተስፋንም የሚያለመልም ነው- -የባሌ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት አገራዊ አንድነትን የበለጠ የሚያጸና ተስፋንም የሚያለመልም ነው- -የባሌ ዞን ነዋሪዎች
ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት አገራዊ አንድነትን የበለጠ የሚያጸና ተስፋንም የሚያለመልም ነው ሲሉ አስትያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የባሌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
የህዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ላይ የነበራቸውን ተስፋ ይበልጥ ያጠናከረ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የባሌ ዞን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የሕዳሴው ግድብ አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ማብሰራቸውን በመገናኛ ብዙሃን መከታተላቸውን አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡
የግድቡ የውኃ ሙሌት በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሙንተሃ ሁሴን፣ ለህዳሴ ግድብ ለአራተኛ ጊዜ ቦንድ በመግዛት ሲሳተፉ በመቆየታቸውና ውጤቱን በማየታቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የግድቡን ጉዳይ ሲከታተሉ እንደነበረ ገልጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የውኃ ሙሌቱን ዜና ማብሰራቸውን ተከትሎ ደስታ እንደፈጠረባቸው ነው የገለጹት።
በቀጣይም በሌሎች አገራዊ የልማት ስራዎች ውስጥ በሙሉ አቅማቸው የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
''የግድቡ ውኃ ሙሌት ብስራት በራሳችን አቅምና ገንዘብ የግድቡ ግንባታ እውን ማድረግ እንደምንችል በተግባር ያሳየ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱልዋሂድ አብዱረህማን ናቸው።
ለግድቡ ግንባታ ባለፉት አራት ዓመታት እስከ 5 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው የሙሌቱን ዜና ሲሰሙ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም ለግድቡ በመንግስትና ህዝብ እየተደረገ የሚገኝ ጥረት እንዲሰምር የጀመሩትን የቦንድ ግዥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ወይዘሮ አለሚቱ ዳኜ በበኩላቸው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከወር ደምወዛቸው በየዓመቱ በ3 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
የአራተኛው ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ኢትዮጵያኖች ከተባበሩና አንድ ከሆኑ የሚያቆማቸው ኃይል እንደሌለ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚጠበቅንን በማድረግ ታሪካዊ አሻራቸውን ለማኖር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የግድቡ የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም መስራት የሚችሉ ብቻም ሳይሆን የጀመሩትን በድል ማጠናቀቅ የሚችሉ መሆናቸውን ያሳየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ ናቸው።
አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ የዞኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በግድቡ ግንባታ ያሳዩት ተሳትፎ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ የታየውን የህዝቡ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር አስተዳደሩ አስፈላጊውን የማነሳሳት ስራ የሚያከናውን መሆኑን አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡
በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ መደረጉን ከዞኑ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፋት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የግድቡን ውሃ ሙሌት ባበሰሩበት ወቅት ''ኢትዮጵያውያን ተባብረን በመሥራታችን ፈጣሪ ረድቶናል፣ በሥራው ውስጥ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ'' ማለታቸው ይታወሳል።