የህዳሴ ግድብ ስኬት በአንድነት ከቆምን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ስኬት በአንድነት ከቆምን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 5 /2015 (ኢዜአ) ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት በአንድነት ከቆምን የማናሳከው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መሰተዳድሩ ፤ የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለያዩ ውጣ ውረዶች አልፎ ለዛሬ የበቃው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ከተባበርንና በአንድነት ከቆምን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
የለውጥ ጉዞ ከጀመርን ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተደቀነባትን በርካታ ፈተናዎች እያለፈች እዚህ መድረሷ የህዝብና መንግስት ጥንካሬን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና ማማ እየገሰገሰች ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በህዝቧና በለውጡ መንግስት ጽናት ማንም ወደኋላ እንደማይጎትታት በተግባር ማሳየቷን ቀጥላለች ሲሉም ተናገረዋል።
ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ማናቸውንም ዓይነት ድጋፍ እስከ ፍጻሜው ድረስ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የክልሉ ህዝብም ለህዳሴው ግድብ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
መጪው ጊዜ ብሩህ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተከናወነው አኩሪ ተግባርም ለክልላችን ህዝብ ና ለመላው ኢትዮጵያውያንእንኳን ደስ አለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።