ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ባሳየነው ህብረትና የዓላማ ጽናት የተገኘው ውጤት በቀጣይ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ጥሩ ማሳያ ነው--አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ባሳየነው ህብረትና የዓላማ ጽናት የተገኘው ውጤት በቀጣይ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ጥሩ ማሳያ ነው--አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ፣ ጰጉሜን 5/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ባሳየነው ህብረት፣ ጥንካሬ እና የዓላማ ጽናት የተገኘው ውጤት በቀጣይ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ጥሩ ማሳያ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ስኬት ማሳያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልክታቸውም "ዓላማና ግባቸውን ጠንቅቀው የተረዱ ትውልዶች በዓባይ ወንዝ ላይ ታሪክ በመስራት 4ኛውን የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት ማጠናቀቅ ችለዋል" ሲሉም ገልጸዋል።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአይበገሬነት ተምሳሌት፣ የጋራ ታሪክ አሻራ እና የትውልዱ ትልቁ ሃውልት መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ደስታ እንዳሉት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ከውስጥም ከውጪም ከባድ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ቢገጥሙም ችግሮችን ተቋቁሞ ጠንክሮ መስራት በመቻሉ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ለማጠናቀቅ ተችሏል።
የለውጡ መንግስት ለሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ትልቅ ትኩረት በመስጠት፣ የህዝቡን ድጋፍ በማጠናከርና የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ግንባታውን ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት ለስኬቱ ሚናው የጎላ እንደነበረም ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ያሳየነው ህብረት፣ ጥንካሬና የዓላማ ጽናት የዓባይን ግድብ እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ብሩህ ማሳያ ነው" ስሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድቡን ጨምሮ እንደሀገር እየተመዘገቡ ባሉ የልማት ውጤቶች የኢትዮጵያ ትንሳኤና የብልፅግና ግብ ሩቅ እንደማይሆን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵውያን አንድነታችን አጠናከረን ለሀገራዊ ስኬት በጋራ ከተጓዝን ማሳካት እንደምንችል የሕዳሴው ግድብ ሕያው ምስክር ነው" ሲሉም አቶ ደስታ ገልጸዋል።
በሕዳሴው ግድብ ያሳየነውን አብሮነት፣ ጥንካሬና የዓላማ ጽናት በሌሎች አገራዊ የልማትና ብልፅግና ዕቅዶች ላይ መድገም ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም 4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ "እንኳን ደስ አላችሁ" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።