ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ አገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ አገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን - የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ ትውልድን በስነ-ምግባር በማነጽ አገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
ሁሉም የትምህርት ተቋማት አገር ተረካቢ ትውልድን የማነጽ በጎ ሚናቸውን በኃላፊነት ስሜት ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን "ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ትውልዱን በስነ-ምግባር አንጾ ለቁም ነገር ማብቃት በሚቻልበት ዙሪያ የሃይማኖት አባቶች ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮርክና አካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ እንዳሉት፤ ቤተ-ክርስቲያኗ ህጻናት በስነ-ምግባር ታንጸው መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ አበክራ እየሰራች ነው፡፡
አገር ወዳድ መልካም ዜጋን መፍጠር የመንግስት ስራ ብቻ ባለመሆኑ ቤተ-ክርስቲያን በጋራ እንደምትሰራ ገልጸው፤ ትውልድን በማነጽና በመገንባት ረገድ የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡም ልጆች ምስጉን ሆነው እንዲያድጉ የራሱን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለበት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሼህ ሁሴን በሽር፤ "አገር የትውልድ ድምር ውጤት ናት" ብለዋል፡፡
ትውልዱ ስርዓት አለብኝነትን እንዲጸየፍ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች መልካም ዜጋን ለአገር ለማበርከት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አባ ዳንኤል ሃሶ በበኩላቸው፤ በቤተ ክርስትያኗ አስተምህሮ ለትውልድ ግንባታ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
አማኞች ልጆቻቸውን በስነ-ምግባር እንዲያሳድጉ ቤተ-ክርስቲያኗ አሰገዳጅ መሪያ አላት ያሉት አባ ዳንኤል፤ ምዕመናንም ትዕዛዙን በማክበር ለተፈጻሚነቱ ጥረት እንደሚያደርጉ አንስተዋል፡፡
በዚህም መልካም ስብእና ያላቸው ህጻናትና ወጣቶችን በማፍራት ለማህበረሰቡና ለአገራቸው የሚጠቅሙ ዜጎችን ለማፍራት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በእድሜ ደረጃ የተከፋፈለ የሰብዕና ግንባታ መንፈሳዊ ትምህርትን የማስተማር ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን መካነ ኢየሱሰ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ ናቸው፡፡
ትምህርት ቤቶችም የትውልድ ግንባታ ሚናቸውን ለማጠናከር የግብረ ገብ ትምህርት ላይ ማተኮር አለባቸው ነው ያለት።
የዘንድሮ የጳጉሜን ቀናት፤ ጳጉሜ 1 የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን፣ ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን በሚል ተሰይመዋል።