ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገባቸውን የመሰረተ ልማቶች አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አደረገ  

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገባቸውን የተለያዩ መሰረተ ልማቶች አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አደረገ፡፡  

በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ከተደረጉት መካከል የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የህፃናት ማቆያ፣ የሠራተኞች ካፍቴሪያና የቢሮ እድሳቶች ይገኙበታል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት፤ በተቋሙ የተገነቡ የመሠረተ ልማቶች ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር ባሻገር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት ያስችላሉ ብለዋል፡፡

የመሰረተ ልማቶቹም ለአገልግሎት መብቃት የመድኃኒቶች ደህንነት ተጠብቆ ኅብረተሰቡ ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የመሰረተ ልማቶች 90 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ገልጸዋል፡፡

የመሠረተ ልማቶቹ ለሰራተኞች ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠርና የተገልጋይ እርካታን ለማስገኘት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ 

በባህርዳርና ሐዋሳ ባሉ የተቋሙ ቅርንጫፎችም መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም  በጅማና በጅግጅጋ መሰል መሰረተ ልማቶች እንደሚከናወኑም ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ተቋርጦ የቆየውን የመድኃኒትና ክትባቶች ማቀዝቀዣ እና ተያያዥ አገልግሎቶች ማዕከል ህንጻ ግንባታን በዛሬው እለት ዳግም አስጀምሯል፡፡  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም