በአዲስ አበባ ከተማ ከመደመር ትውልድ መጽሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ ከመደመር ትውልድ መጽሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ከመደመር ትውልድ መጽሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ፡፡
በመላ ሀገሪቱ "ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር" በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም የትውልድ ቀን እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዛሬው እለትም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከመደመር ትውልድ መጽሃፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በስፋት በመገንባት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሰባት የህጻናት መጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት ደግሞ አምስት ማዘውተሪያዎች መመረቃቸው ተናግረዋል፡፡
ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ስፍራዎቹ ሀገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸው ሃብቶችን በአግባቡ እንዲጠብቋቸውና እንዲጠቀሙባቸው መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።
የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ንጋቱ ዳኛቸው፤ ከመደመር ትውልድ መጽሃፍ ሽያጭ በተገኘ 30 ሚሊየን ብር የህጻናት መጫወቻና ደረጃውን የጠበቀ ማዝወተሪያ መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።
ኢንተርናሽናል የቴኳንዶ አሰልጣኝ ሳቦን ቢላል አሕመድ፤ በበኩሉ የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች የተሰጠው ትኩረት አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም የከተማዋ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያዘወትሩ ምቹ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ትውልዱን በስፖርትና ስነምግባር ለማነጽ የተጀመረው ስራ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ከንቲባዋ ለወጣቶች የስፖርት ቁሳቁስና ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተዋል።