ቀጥታ፡

4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ በጋራ ከተሰለፉ የትኛውም ፈተና እንደማያቆማቸው ያመላከተ ነው- ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስራ በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ በጋራ ከተሰለፉ የትኛውም ፈተና እንደማያቆማቸው ያመላከተ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡

በግድቡ ግንባታ የተመዘገበው ስኬት በትብብር ሌሎች ታላላቅ የልማት ስራዎችን አውን ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ዛሬ አብስረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው "በገንዘባችሁ፣ በዕውቀታችሁ፣ በጉልበታችሁ እና  በጸሎታችው በሥራው ውስጥ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ።" በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ያሳዩትን ትብብር በሌሎች የልማት ስራዎችም መድገም እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የ4ተኛው ዙር ውሃ ሙሌት በሚመለከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ ባለፉት አራት ዓመታት የውሃ ሙሌት ስራውን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የዝናብ መጠን መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የውሃ ሙሌት ስራው በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት በማያደርስ መልኩ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነትም በዘንድሮው ክረምት በግብጽ የሚገኘው የአሰዋን ግድብ ከበቂ በላይ ውሃ በመያዙ ምክንያት በግድቡ ማስተንፈሻ አማካኝነት ውሃ የማፋሰስ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስቱ አገራት የትብብር ምንጭ ከመሆን ባሻገር በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚያስከትለው ጉዳት እንደሌለ በተግባር ያመላከተ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ ኃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች በስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሌሎች ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው የተናገሩት፡፡

4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በግድቡ ግንባታ ሂደት ሌላኛውን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ የተናገሩት፡፡

"ከዚህ በኋላ የሚኖሩ ስራዎችም ከዚህ ቀደም ካለፍንባቸው የተሻሉ ይሆናሉ፤ ይህም ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ስኬት ነው" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ያላቸውን ሃብት ሳይሰስቱ ማበርከታቸውን አስታውሰው፤ ይህም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያዊያን በትብብር ታላላቅ የልማት ስራዎችን እውን ማድረግ አንደሚችሉ ያመላከተ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም በትናንሽ ጉዳዮች ከመለያየት ወጥተን ለኢትዮጵያ ልማት በጋራ መሰለፍ አለብን ነው ያሉት፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም