ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ለመገንባት መምህራን ሚናቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ-የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ለመገንባት መምህራን ሚናቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ-የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ ለመገንባት መምህራን ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ገለፀ።
የመምህራንን ትውልድን የማነፅ ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ ማሕበረሰቡ፣ የሐይማኖት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን ''ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር'' በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በትውልድ ግንባታ ሒደት ውስጥ መምህራን ያላቸውን ሚና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲን አነጋግሯል።
ዶክተር ዮሐንስ እንዳሉት፤ ከአጸደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ መምህራን ትውልድን በቅብብሎሽ በመገንባት ሂደት የማይተካ ሚና አላቸው።
ትውልድን በሞራልና በእውቀት በአግባቡ መቅረፅ ለሀገር ግንባታ መረጋገጥ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ፤ ለዚህ ስኬት መምህራን ሃላፊነታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የማሕበሩ ፕሬዝዳንት አክለውም አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የታለመውን ግብ እንዲያሳካ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ በተለይ መምህራን ትልቅ ሚና ይወጣሉ ነው ያሉት።
የትውልድ ግንባታ ስራ የሁሉንም ዜጋና ተቋማት ጥረት እንደሚፈልግም ዶክተር ዮሐንስ አንስተዋል።
በመሆኑም ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ የትምህርት ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት ሀገርን ተረክቦ ወደ ከፍታ የሚያሻግር ትውልድ በአግባቡ በመቅረፅ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።