ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የመላው ኢትዮጵያውን የጋራ ጥረት ውጤት ነው--አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፣ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)-የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁ የመላው ኢትዮጵያውን የጋራ ጥረት ውጤት ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የሕዳሴው ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የግድቡ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ለዘመናት የቆየው የኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት እውን እንዲሆን ጉልህ አስተዋጾ አለው።

የግድቡ መሞላት ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ በማለፍ ግድቡን ጥቅም ላይ ማዋል እንደምትችል በተግባር ያሳየችበት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም አቶ ኡሞድ አስረድተዋል።

የግድቡ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የመላው ኢትዮጵያውን የጋራ ጥረት ውጤት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በጋራ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑንም አመልክተዋል።

በቀጣይም ለሀገራዊ የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያውያን በጋራ ተባብረን መስራታችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል። 

ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደአገልግሎት እንዲገባ የክልሉ ህዝብና መንግስት የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የክልሉ ህዝብና እና ኢትዮጵያዊያን የግድቡ የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም