የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ አራተኛ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ኩራት ተሰምቶናል -የኮንሶ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ አራተኛ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ኩራት ተሰምቶናል -የኮንሶ ዞን ነዋሪዎች
ካራት ፤ጳጉሜ 05/2015 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ አራተኛ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮንሶ ዞን ነዋሪዎች ደስታቸውን ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አማኑኤል ግርማ እንዳሉት 4ኛዉ ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያበስሩ ኩራት ተሰምቷቸዋል።
"ኢትዮጵያ በርካታ ተጽእኖዎችን ተቋቁማ የግድቡ ግንባታና የውሀ ሙሌቱ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህዝቦቿ አዲስ ታሪክ ያስመዘገብንበት ነው" ብለዋል ።
"ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ህዝብ እየተገነባ ያለ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው" ያሉት አቶ አማኑኤል "ግድቡ የሀገራችንን የዕድገት ጉዞ ከማሳለጥ ባለፈ ለታችኞች ተፋሰስ ሀገራትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኛል" ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስተው ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁንም ለግድቡ ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል ።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ አብርሃም አበበ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ልዩ ደስታ የፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል ።
ለግድቡ ግንባታ ሦስት ጊዜ የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው በቀጣይም የሚፈለገውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል ።
"የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝብ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ የኮንሶ ዞን ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ኮማንደር ተስፋዬ ገሌቦ ናቸው።
የግድቡን የአራተኛ ዙር ውሀ ሙሌት ብስራት ሲሰሙ ወኔና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ለግድቡ ግንባታ ሶስት ጊዜ በደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት እና በ8100 A እና በልዩ ልዩ የድጋፍ መንገዶች አስተዋጽኦ እያደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
"ግድቡ በጨለማ ውስጥ ለሚኖረው ወገናችን ብርሀን በመሆኑ በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ ሀገራት የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው "ለአፍሪካውያን ጭምር ኩራት ነው" ሲሉ አብራርተዋል።