ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ድል ማሳያ ነው - ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ውስጣዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ድል ማሳያ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ገለጹ።

ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያዊያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል ተመራማሪው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ዛሬ አብስረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ በጉልበትና በጸሎት ተባብረው በመስራታቸው የተገኘ ስኬት መሆኑን በማንሳት እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

በግድቡ የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ አንድምታ ዙሪያ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ እንዳሉት፤ ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ ጥረታቸው እያሳኩት የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

የግድቡ አራተኛ ዙር ሙሌትም  በገንዘብ፣ በጉልበትና በጸሎት እያገዙ ለሚገኙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ግድቡን ቀን ከሌሊት ለሚጠብቁ የፀጥታ ሃይሎች፣ ሀሩር ተቋቁመው ግንባታውን ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ላስገነዘቡ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ከታላቁ የአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያዊያን  የፖለቲካ አስተሳሰብ፣  ኢኮኖሚያዊ ልዩነት፣ እንዲሁም ቋንቋና ሃይማኖት ሳይገድባቸው ዳግም የተሰባሰቡበት  የኩራት ካስማ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚጥል መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው፤ አራተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቁ ትርጉሙ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የግድቡ ግንባታ ከጅምር እስከ አሁን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ አልፎ በመገባደድ ላይ መሆኑም ኢትዮጵያ በፅናት እየተሻገረች ስለመሆኗ ምልዕክት ነው ብለዋል።

በግድቡ ዙሪያ ከፍተኛ ውጫዊ ጫና እንደነበር በማንሳት፤ ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ጥቅም አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ግድቡን እየገነባች መሆኑን በማስረዳት ጫናውን መቀልበሷን ተናግረዋል።

በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ውሃውን ለብቻችን እንጠቀም የሚሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ያላሳተፉ የቅኝ ግዛት ውሎች ዳግም ለማጽናት የዓረብ ሊግን በመጠቀም ዘመቻዎች ሲደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችለዋል ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት በተያዘው ጊዜ መሞላቱም፤ ሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርቷ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ አቅም እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀጣይም ከግድቡ በሚገኘው የኃይል ምንጭ ጠንካራ የማህበራዊ ተቋማትን ለመገንባትና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር እንደሚያግዝም ነው ያነሱት።

ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለአፍሪካ ቀንድና ለተፋሰሱ ሀገራት መረጋጋትና የጋራ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ሁሉ የግድቡ ሙሌት ትልቅ ዜና መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓባይን በማልማት ሂደት ውስጥ ብዙ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገች ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ የህዳሴ ግድብን በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ የሞከሩና የግጭት መነሻ ሊያደርጉ ሲሰሩ የነበሩ አካላትን ሴራ ማክሸፏን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን መርህን ባከበረ መልኩ እየተገበረች ስለመሆኗ እውነታውን ለዓለም በማስረዳትን የተዛቡ አካሄዶችን መቀልበሷን ተናግረዋል።

በተለይም የዓባይ ተፋሰስ የጋራ ልማት እንጂ የግጭት መንጭ መሆን የለበትም የሚለው አቋሟ ብዙዎች ቆም ብለው እንዲያዩ ማድረጉን ነው ያብራሩት።

አሁንም በዲፕሎማሲው መስክ ትላልቅ የቤት ስራዎች እንዳሉ የጠቀሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ የትብብር ማዕቀፉን ያልፈረሙ ሀገራትን በማስፈረም የዓባይ ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋም ለማድረግ ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ውስጥ ካላት ትልቅ ተሰሚነት አኳያ ፖለቲካዊ ሚና መወጣት አለባት ብለዋል።

ከዓባይ ተፋሰስ የውሃ አጠቃቀም አንጻር የዘመኑን የዲፕሎማሲ ከፍታ ለማስመዝገብም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም