ቀጥታ፡

ሀገር ተረካቢና መልካም ስነምግባር ያለው ትውልድን መገንባት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው -የአጸደ ህጻናት መምህራን

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2015(ኢዜአ)፦ህጻናትን በበጎ ስነምግባር ቀርጾ ማሳደግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የአጸደ ህጻናት መምህራን ገለፁ፡፡ 

ትውልድን የመቅረፅ ኃላፊነት የተሰጣቸው፣  እውቀትና የባህሪ ለውጥን በንድፈ ሀሳብና በተግባር አጣምረው የሚያስጨብጡ የሀገር ባለአደራ ናቸው መምህራን።

በዚህ ሚናቸው የተነሳም አንዳንዶች “የትምህርት ስርዓት ምሰሶዎች” ይሏቸዋል።

በተለይም የአጸደ ህጻናት መምህራን የትውልድ ንጹህ አዕምሮ ላይ የሚያሳርፉት የእውቀት፣ የስብዕናና ማህበራዊ እድገት አሻራ ቀላል የሚባል አይደለም።

በዚህም በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የነገ አገር ተረካቢዎችን በመቅረፅና መልካምነትን በማንበር የማይተካ ሚና ይጫወታሉ።

ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን "ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

ቀኑን በማስመልከትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተለያዩ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት መምህራንን ስለ ትውልድ ግንባታ አነጋግሯል።

በአፄ ፋሲል አፀደ ህፃናት ትምህርት ቤት ለ17 ዓመታት በመምህርነት ያገለገለችው አዲስ ወርቁና አሁን ላይ በዚሁ ትምህርት ቤት እያስተማረች ያለችው ሰላማዊት ወንድሙ "ህፃናትን ማስተማር ጥንቃቄ የሚፈልግና ድካም ያለው ቢሆንም ለህሊና የሚሰጠው ደስታ ወደር የለሽ ነው" ብለዋል።


 

ከቀለም ትምህርት ባለፈ ምስጉን ስነምግባር ያላቸው፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ወላጆቻቸውንና  መምህራንን የሚያከብሩ አድርገው እየቀረጹ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የህጻናትን ባህሪ በአግባቡ መቅረፅና ስለ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ስለሀገር ፍቅር፣ ስለበጎነት መልካም ነገርን  በንጹህ አዕምሯቸው ላይ ማስረፅ የሁሉም ማህበረሰብ ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።


 

በአሚጎንያን አፀደ ህፃናት ከአሥር ዓመታት በላይ በመምህርነት ያገለገሉት ቤተልሔም ተሾመና ትዕግስት አስቻለው መምህራን ለህፃናት በሁሉም ነገር አርአያ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። 

"አፀደ ህፃናት" ቀጣይ ትውልድ የሚቀረፅበት መሠረት ስለሆነ በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት የሚሰራ እንደሆነ ይገልፃሉ።


 

በተለይም ህጻናቱ ያሉበት የእድሜ ደረጃ የመምህራንን ድርጊትና እንቅስቃሴ ወደ አዕምሯቸው በቀጥታ የሚቀበሉበት በመሆኑ፤ መምህራኑ በፍቅርና በመልካምነት ማስተማር እንደሚገባቸው መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም