ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንድትሆን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንድትሆን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንድትሆን በዘርፉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ልጆች የስፔስ ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል ለሦስት ተከታታይ የክረምት ወራት ያሰለጠናቸውን 50 ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ልጆች ያላቸውን ተሰጥኦ መነሻ በማድረግ ለቴክኖሎጂ ቅርብ እንዲሆኑ ተከታታይ ሥልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም እንደ የኢትዮጵያ ልጆች የስፔስ ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል ያሉ ተቋማትን ማስፋት እንደሚገባ ገልጸው ታዳጊዎች ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ያላቸውን ተሰጥኦ በማውጣት ነገ አገርን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ልጆች ሕልማቸውን ዕውን እንዲያደርጉና ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንድትሆን የበኩላቸውን መወጣት እንዲችሉ የታዳጊዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልጆች የስፔስ ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው እንደ አገር ያልተፈቱ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው በማዕከሉ የሚሰለጥኑ ታዳጊዎችን ቁጥር የማሳደግ ሥራ በቀጣይ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በተመራቂ ተማሪዎች የተሰሩት የፈጠራ ሥራዎች ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ታዳጊዎቹን የማገዝና ይበልጥ የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ሮቤል በአምላክና አምላክበቃሉ ተሰማ፤ በሥልጠናው ያገኙትን አውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ችግር ፊቺ ሊሆን የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የጀመሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች በማጠናከር ለአገሪቱ ልማትና እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።