መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገለት
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፡- መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገለት።
ድጋፉን ያደረጉት ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕና ኅብረት ባንክ ናቸው።
ተቋማቱ ያደረጉትን የገንዝብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራች የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ዛሬ አስረክበዋል።
በዚህም የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ማኔጅመንትና ሠራተኞች የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የምግብ፣ አልባሳትና የእርድ ከብት አበርክተዋል።
የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ድርጅቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
ለመቄዶኒያ የተደረገው ድጋፍ የተቋሙ ሠራተኛ ከማኔጅመንቱ ጋር በመሆን ያደረገው መሆኑን ጠቁመው ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ የኅብረት ባንክ ማኔጀመንትና ሠራተኞች የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብና የተለያዩ አልባሳትን ለማዕከሉ በስጦታ አበርክተዋል።
የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ከበደ ባንኩ የሚጠበቅበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በተለያዩ ጊዜያት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራችና ስራ አስኪያጅ የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ በዚህ ወቅት ጊፍት ቢዝነስ ግሩፕና ኅብረት ባንክ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።
ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር በመከተል ሌሎችም አካላት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።