ቀጥታ፡

ሰራዊቱ የአገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን አምራች የልማት ኃይል መሆኑንም በተግባር እያሳየ ነው - የአየር ኃይል አባላት

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፦  ሰራዊቱ የአገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን አምራች የልማት ኃይል መሆኑንም በተግባር እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ገለጹ።

አየር ኃይሉ የአገርን የአየር ክልል ከማስከበር በተጨማሪ የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመወጣት ላይ ነው።

በአደጋ ወቅት ዜጎችን በመታደግ ፣ የአየር አምቡላንስ አገልገሎት በመስጠት፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በልማት ተግባራት በመሳተፍ ሕዝባዊነቱን በማሳየት ላይ ይገኛል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩም የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን የስንዴ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጓሮ አትክልቶችን የማልማት ሥራም እያከናወነ ነው።

የአየር ኃይል ፋይናንስ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ኮሎኔል በሻህ ደገፋ ተቋሙ በተለያዩ አካባቢዎች ክፍት ይዞታዎችን በማልማት ሰራዊቱንና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በዚህም በግቢው ያለውን ሰፊ ቦታ ተጠቅሞ በማረስና ስንዴ በመዝራት ግቢውን ከማስዋብ ባለፈ በሚገኘው ምርት ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ በሚገኝበት ቢሾፍቱ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በልማት ሥራው እየተጠቀሙ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ሰራዊቱ ከተሰጠው ተልዕኮ ጎን ለጎን የአገር ሉዓላዊነት ጠባቂ ብቻ ሳይሆን አምራች የልማት ኃይል መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሕዝብ ግንኙነትና የሄሊኮፕተር አብራሪ ሻለቃ ሰዒድ ደሳለኝ በበኩላቸው ተቋሙ የሚገኝበት ጫካ ለምንም አይነት አገልግሎት ሳይውል ተቀምጦ እንደቆየ አስታውሰዋል።


 

ይሁንና ተቋሙ ጫካ የነበረውን ቦታ ወደ ልማት በመቀየር ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝና የልማት እንቅስቃሴ ለሌሎች ተቋማት አርዓያ የሚሆን መሆኑን ጠቁመዋል።

ያለሙ ክፍት ቦታዎችን በማልማት ኢትዮጵያ አምራችነቷን በማሳደግ በምግብ ራስ ለመቻል የምታደርገውን እንቅስቃሴ መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከ94 ዓመት በፊት በአፍሪካ የመጀመሪያ አየር ኃይል ሆኖ የተመሰረተ አንጋፋ ተቋም ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም