የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባለአደራ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀላችን የላቀ ኩራት ይሰማናል - መሰረታዊ ወታደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባለአደራ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀላችን የላቀ ኩራት ይሰማናል - መሰረታዊ ወታደሮች
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባለአደራ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀላችን የላቀ ኩራት ይሰማናል ሲሉ የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምሩቃን መሰረታዊ ወታደሮች ተናገሩ።
የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለተከታታይ ስድስት ወራት በወታደራዊ ጥበብ ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች አስመርቋል።
በዚሁ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ምሩቅ መሰረታዊ ወታደሮች የአገር ፍቅር ስሜት የመከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
መሰረታዊ ወታደር ኤፍሬም እሰዬ፤ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ የመጨረሻው የሉዓላዊነት ባለአደራ ተቋም ነው ብሏል።
ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀሉ የላቀ ኩራት እንደሚሰማው በመጠቆም፤ በቀጣይም የሚሰጠውን ግዳጅ በሚገባ በመፈጸም ለአገር ሰላምና ደህንነት በታላቅ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጿል።
ሌላኛው መሰረታዊ ወታደር አማረ ሉሌ፤ ጀግናውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በመቀላቀሉ ደስታ እንደሚሰማው ገልጿል።
በስድስት ወራት የማሰልጠኛ ቆይታቸው ያገኘው የአካል ብቃት ስልጠናና የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ኢትዮጵያዊ ስብዕና እንዲላበስ እንዳደረገው ተናግሯል።
መሰረታዊ ወታደር አብርሃም ሙሉጌታ የተሰጣቸው ስልጠና ግዳጃቸውን በብቃት በመወጣት ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪና ከውስጥ አፍራሽ ሀይሎች ለመጠበቅ ዝግጁ እንዳደረጋቸው ገልጿል።
በስድስት ወራት ቆይታችን ኢትዮጵያና ህዝቦቿን በታማኝነት ማገልገል የሚያስችል ወታደራዊ ጥበብ የተሞላበት ስልጠና ስንከታተል ቆይተናል ያለው ደግሞ መሰረታዊ ወታደር ሲሳይ ለገሰ ነው።
በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የ3ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ 4ኛ ሻምበል አዛዥ መቶ አለቃ ጫልቱ ገመቹ፤ መሰረታዊ ወታደሮቹ ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚስችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ 2ኛ ሻምበል 2ኛ መቶ መሪ ሀምሳ አለቃ አዛሪያስ ዮኃንስ በበኩላቸው ምሩቃኑ ብቁ የሚያደርጋቸው የአካል ብቃትና የቴክኒክ ስልጠና ሲሰጣቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
በምርቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንን ጨምሮ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተመራቂ ቤሰቦችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ለተከታታይ ስድስት ወራት ሲሰጥ በነበረው ወታደራዊ ስልጠና የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞች እና ሌሎች ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።