ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን በማዳኑ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው - የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን በማዳኑ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው - የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ
ሀዋሳ ፤ ጳጉሜን 04/2015 (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን በማዳኑ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለፁ ።
ፓርኩ በ2015 ዓ.ም ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 54 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቱም ተገልጿል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሽግግር ስኬታማነት የላቀ ሚና ኢንዲኖረው በማድረግ ፓርኩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአምራችነት ቀን ''ከሸማችነት ወደ አምራችነት'' በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን 04 ቀን ታስቦ መዋሉ እንደ ሀገር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ ጠቅሰው በሁሉም ዘርፍ አምራች ዜጎችን በማፍራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢኮኖሚ፣ በማህበረሰብ ተጠቃሚነት እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ እመርታ ለማምጣት በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ አየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይ ምርቶችን ወደ ዓለም ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ዋነኛ ተልዕኮው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 54 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደተቻለ አስረድተዋል።
ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በሚደረገው ጥረትም ፓርኩ የራሱን አሻራ እያኖረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ለአብነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አልባሳት ከዚህ በፊት በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ይመጣ እንደነበር ጠቅሰው ፓርኩ ከሌሎች ፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በውስጡ የሚገኙ ኩባንያዎች እንዲያመርቱ በማድረግ የምርት መተካትና የውጭ ምንዛሪን የማዳን ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች በውጭ ገበያ ስታንዳርድ የሚያመርቷቸውን ሌሎች አልባሳትንም ጭምር በመንግስት በተቀመጠላቸው በየስድስት ወሩ የሚታደስ የፈቃድ መመሪያ መሠረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ፓርኩ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሌሎች ምርቶች ከሚቀይሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚው መነቃቃት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ ያለውን አቅም በመጠቀምና በጥሬ ዕቃ አቅራቢነት የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን አቅም በመገንባት ምርቶች ከገበሬው ደጃፍ ጀምሮ ወደ ውጭ እስከሚላኩበት ድረስ ያለውን ሂደት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በመሸፈን ለጥሬ ዕቃ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ለዚህም ፓርኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በተለይ በጥጥ ምርት ላይ እመርታን የማምጣት ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት አኳያ ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ25 ሺህ በላይ ሰራተኞች በውስጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ፓርኩ ከክህሎት ሽግግር አኳያ እያበረከተ ያለው አስተወፅዖ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ማቴዎስ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ገቢ ከማግኘት ባሻገር የቴክኖሎጂውን አለም በቀላሉ እንዲቀላቀሉ መንገድ እንደከፈተላቸው አስረድተዋል።
ፓርኩ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ተማሪዎች የተግባር ሥልጠናዎችን የሚያገኙበትን እድል በማመቻቸት በሰው ሀይል ልማት ላይ የሚጠበቅበትን አስተዋጾዖ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ኢንጆ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ በኤክስፖርት ስታንዳርድ የሚያመርታቸውን አልባሳት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ የኦፕሬሽናል ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም መብራቱ ገልፀዋል።
የተለያየ አይነት ያላቸው ሸሚዞች ፣ ቲሸርቶችና ሌሎች ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ኤፍሬም የተለያዩ ክልሎች የፖሊስ አልባሳትን አምርተው ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።