የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካነ አመራር ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካነ አመራር ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2015(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካነ አመራር ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሕብረት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ ተናገሩ።
የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ በ8ኛ ዙር አጭር ኮርስ የሰለጠኑ ከፍተኛ መኮንኖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ኮሌጁ ዛሬ ያሰመረቃቸው 37 ከፍተኛ መኮንኖች፤ ላለፋት ሶስት ወራት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሥልጠናቸውን በብቃት ያጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
ተመራቂዎች በሥነ-ምግባር፣ በወታደራዊ ጥበብ፣ በሙያዊ ብቃትና በላቀ ዝግጅት የሰራዊት አባላትን ለመምራት የሚያስችላቸውን እውቀትና ከህሎት ገብይተዋል ተብሏል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የመከላከያ ሕብረት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ እንደተናገሩት ተቋሙ ከሚያካሂደው የሰራዊት ግንባታ ሪፎርም ውስጥ አንዱና ዋነኛው በየደረጃ ያለውን አመራር አቅም ማጎልበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ከዘመኑ እድገትና ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ የሚሄድ በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካነ አመራር ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የሚያበቃ ማንኛውንም ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው የዝግጅታችንም ትኩረት ማንኛውንም አይነት ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል አቅም መገንባት ነው ብለዋል።
ይህ ደግሞ ከሰው ኃይል ግንባታ ጀምሮ በሁሉም ውጊያዎች አቅምን ማሳደግን እንደሚያካትት ተናግረው አቅምን ማጎልበት ጠንካራና አይነኬ ሃይል አድርጎ ማዘጋጀት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር የዛሬ ተመራቂዎች የወሰዱትን ወታደራዊ ትምህርት በአውደ ውጊያ ካካበቱት ዕውቀትና ልምድ ጋር በማቀናጀት ግዳጃቸውን ለመፈጸምና የበለጠ ተልዕኮ ለመወጣት እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቻው በበኩላቸው፤ የሠራዊቱ ቁልፍ ተልዕኮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በመጠበቅ የመጨረሻ ምሽግ በመሆን ማገልገል ነው ብለዋል።
ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት መከላከያ በሰው ሃብት ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮሌጁ የትምህርትና ሥልጠና ሂደት የበለጠ በማጎልበት የተቋሙን የፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ በማፋጠን ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አመራሮችን በማፍራት ረገድ የተሰጠውን ተልእኮ አየተወጣ ነው ብለዋል።
ትምህርትና ሥልጠና የፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ አንድ ዘርፍና በየደረጃው እየጎለበተ የሚሄድ ከዘመናዊ ትጥቅና ቴክኖሎጂ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሥራ በመሆኑ በዚህ ረገድ ኮሌጁ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቁ ከፍተኛ መኮንኖች በበኩላቸው ያገኙትን የአመራር ጥበብ በማጎልበት ከዚህ በፊት በአውደ ውጊያ ካካበቱት ዕውቀትና ልምድ ጋር በማጣመር ለበለጠ ግዳጅና ሃላፊነትን ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።