ቀጥታ፡

የውትድርና ሙያ የሀገር ፍቅር የሚገለጽበት የብዙ ሙያና የታላላቅ ሰዎች መሰረት ነው - ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን

 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2015(ኢዜአ)፦ የውትድርና ሙያ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገለጽበት የብዙ ሙያና የታላላቅ ሰዎች መሰረት መሆኑን የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ገለጹ።

የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በወታደራዊ ጥበብ ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች አስመርቋል።

በዚሁ ወቅት የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን፤ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ዘመናዊ ሰራዊት በመገንባት ተልዕኳቸውን በጀግንነት እየተወጡ ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመፋለም አገሩን ከጫፍ ጫፍ በመጠበቅ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሰራዊቱ ላይ የሚነሱ ስም የማጥፋት መሰረተ-ቢስ ክሶችም በሰላም ወዳድ የኢትዮጵያ ህዝብ እየከሸፉ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮም ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆንን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቁርጥ ቀን ልጆቿ አኩሪ መስዋትነት ክብር እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች አገር መሆኗን ገልጸዋል።

በትውልድ ቅብብሎሽ የተገኘውን የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ ለማስቀጠልም በጽኑ ዲሲፖሊን የሚመራ የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ለዚህም አስፈላጊውን የሰው ሃይል ልማትና ስልጠና በማስፋት ለመከላከያ ሰራዊት ግንባታ አቅም የሚሆን ሃይል እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።

የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ በስሩ በሚገኙ የማሰልጠኛ ጣበያዎች የሰራዊቱን የግዳጅ አፈፃጸም ለማሳደግ ሰፋፊ ተግባራትን እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በጦላይ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ መሰረታዊ ወታደሮችም የስነ-ልቦና፣ የአካል ብቃት እና ሌሎች ትምህርቶችን በብቃት በመወጣት ስልጠናቸውን በድል አጠናቀዋል ብለዋል።  

መሰረታዊ ወታደሮቹ በቂ የስልጠና ጊዜ ተሰጥቷቸው በተቀመጠው መደበኛ የስልጠና መርሃ-ግብር መሰረት ስልጠናውን በብቃት እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል።

የውትድርና ሙያ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገለጽበት የብዙ ሙያ እና የታላላቅ ሰዎች መነሻ መሰረት ነው ያሉት ኃላፊው፤ ምሩቃኑም የአገር ኩራት ወደሆነው ተቋም በመግባታቹህ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።

በስልጠናው ያገኙትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመጠቀም በሚመደቡበት የስራ ክፍል የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ በመወጣት በታላቅ አገራዊ ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። 

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጡምሲዶ ፊታሞን፤ አገር ታፍራና ተከብራ ሉዓላዊ አንድነቷን የምታስቀጥለው አኩሪ መስዋትነት የሚከፍል ጀግና ሰራዊት መገንባት ስትችል ነው ብለዋል።

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱም የኢትዮጵያ ዘብ መሆን የሚያስችል ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ለመቅሰም የወሰኑ ጅግኖችን ሲያሰለጥን መቆየቱን ገልጸዋል።

ሰልጣኞቹ ለውትድርና ብቁ የሚያደርጋቸው ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና ተሰጥቷቸው ለምረቃት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።

በምርቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም