ችግር ፈቺ ፈጠራ

508

ባስልኤል የእንጨትና ብረታ ብረት ማህበር በጅንካ ከተማ በክላስተር ማዕከል ውስጥ ከተደራጁ 8 ማህበራት አንዱ ነው ። 

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ሙሐመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ማህበሩ ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ባገኘው 450 ሺህ ብር የብድር ድጋፍ በ2007 ዓ.ም ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል። 

ከብድር አቅርቦቱ በተጨማሪ በመንግስት የማሽነሪ እና የማምረቻ ሼድ ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል። 

ማህበሩ ከሚያመርታቸው የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤቶች በተጨማሪ ከውጪ በከፍተኛ የዶላር ምንዛሪ የሚገቡ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ያመርታል። 

ማህበሩ ካመረታቸው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች አንዱ የጥልቅ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን ይጠቀሳል። 

ቀደም ሲል ማሽኑን ለመግዛት እስከ 2 ሚሊዮን ብር ይፈጅ እንደነበር የገለፁት የማህበሩ ሰብሳቢ ፤ ይህንኑ ማሽን በተሻለ ጥራት ማምረት በመቻላችን ለማሽኑ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ማዳን ችለናል ብለዋል። 

የጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኑንም በጅንካ ከተማ ለሚገኙ ለተለያዩ ተቋማት በተመጣጣኝ ዋጋ የጥልቅ ጉድጓድ በመቆፈር የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራቸውን መቅረፉንም ነው አቶ ጌታቸው የሚናገሩት። 

በተጨማሪ ኃይል ቆጣቢ የእህል ወፍጮ፣ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ፣ በሰአት እስከ 10 ኪሎ ግራም ቡና የሚቆላ ማሽን፣የገብስ መፈተጊያና የአተር መቁያ ማሽን በአገልግሎት ላይ ከሚገኙ የማህበሩ የፈጠራ ውጤቶች ይጠቀሳሉ። 


 

ከተጠቀሱት ምርቶች ባለፈም ማህበሩ በሚሰራቸው የብረት ማቅለጫና ቅርፅ ማውጫ ማሽኖች የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችንም ያመርታል። 

የማህበሩ የረጅም አመታት ደንበኛ እንደሆኑ የሚገልጹት የጅንካ ከተማ ነዋሪ አቶ አወቀ አይኬ፤ ''ማህበሩ የሚሰራቸው አዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች የማህበረሰቡን ችግር በእጅጉ እያቃለሉ ናቸው'' ብለዋል። 

ከዚህ ቀደም የተሽከርካሪ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማግኘት 730 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄዱ አስታውሰው አሁን ማህበሩ የምንፈልገውን ብሎንም ሆነ ሌሎች የመለዋወጫ ዕቃዎችን በፈለግነው ዲዛይን እዚሁ አምርቶ በማቅረቡ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የምናባክነውን ጊዜና ገንዘብ እንድንቆጥብ አስችሎናል ብለዋል። 

በተለይ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኑ በከተማዋ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከማቃለል አኳያ ትልቅ ሚና እየተወጣ እንዳለም ተናግረዋል። 


 

ወይዘሮ ትዕግስት አባይነህ የተባሉ የጅንካ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ማህበሩ የፈጠራቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በተለይ የሴቶችን ድካም በእጅጉ እንዳቃለለ ተናግረዋል። 

ቀደም ሲል ገብስ ለመፈተግ፣አተር ለመቁላት እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን ለማዘጋጀት ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበር ገልፀው ይህም ከቢሮ የስራ ሰአት ውጪ ባለው ትርፍ ጊዜ ለማከናወን አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል ። 

በተለይ በቤት ውስጥ የበአልና ሌሎች ፕሮግራሞች ሲኖሩ እነኚህን ስራዎች መስራት አድካሚ እንደሆነ ገልፀው አሁን  ማህበሩ በፈጠራቸው ዘመናዊ ማሽኖች አድካሚ ስራዎችን ግማሽ ሰአት ባልሞላ ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል ። 

ማህበሩ የሰራቸው ወጪ ቆጣቢ ምድጃዎችም በቤት ውስጥ ምግብ ለማዘጋጀት አመቺና ጥራታቸውም ወደር እንደሌለው የገለፁት ወይዘሮ ትዕግስት እነዚህ ምርቶች በእጅጉ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉና ህይወትን ቀለል የሚያደደርጉ በመሆናቸው እንዲህ ያለ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ግለሰቦች ሊበረታቱ እንደሚገባም ተናግረዋል ። 

የባስልኤል የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ማህበር ከማህበሩ አባላት በተጨማሪ ለ8  ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል፤ ቀደም ሲል በማህበሩ ይሰሩ የነበሩ አባላትም ከማህበሩ በቀሰሙት ዕውቀትና ልምድ የግል ድርጅት በመክፈት የራሳቸውን ገቢ እያመነጩ ለሌሎችም የሥራ ዕድልን ፈጥረዋል። 

በማህበሩ ተቀጥረው ከሚሰሩ ባለሙያዎች አንዱ አቶ ደረጀ ሙሐመድ ሲሆኑ በማህበሩ ውስጥ በመስራታቸው ተጠቀሚነታቸው የደሞዝ ብቻ እንዳልሆነና የዕውቀት ሽግግር ዕድልን ተጠቃሚ እንደሆኑ ያነሳሉ።

ታዲያ የነዚህ የፈጠራ ሀሳቦች ባለቤት የሆነውና የማህበሩ መስራች አቶ ጌታቸው ሙሐመድ ይህን የፈጠራ ሀሳብ በማፍለቅ እውን የሚያደርገው እንደ ሙሉ ጤነኛ ሰው በእግሩ እንደ ልቡ እየተንቀሳቀሰ ሳይሆን በዊልቸር እየተገፋ ነው። 

አቶ ጌታቸው በ1990 ዓመተ ምህረት በድሬዳዋ ከተማ በስራ ላይ ባጋጠመው የኤሌክትሪክ አደጋ ከፎቅ ላይ በመውደቁ በእግሮቹ ላይ ጉዳት ሊደርስበት መቻሉን ተናግሯል። 

አደጋው ካጋጠመው ጊዜ አንስቶ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፉን አስታውሶ ለፈተናዎች እጅ ባለመስጠቱ ለዚህ ስኬት መብቃቱን ይናገራል። 

''ያጋጠመኝን የተሽከርካሪ ችግር ለመቅረፍ የወዳደቁ ሞተር ሳይክሎች በመጠገን ለራሴ እንድትመቸኝ አድርጌ የሰራኋት ተሽከርካሪ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ አድርጋኛለች'' ብለዋል። 

ማህበሩ አሁን ላይ ከቋሚ ንብረቶች በተጨማሪ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብትእያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አቶ ጌታቸው ገልጿል። 

በቀጣይም እንደ አገር በተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በውድ ዋጋ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በተሻለ ዲዛይን በማምረት የውጭ ምንዛሪውን ለማስቀረትና  የማህበረሰቡንም ችግር ለማቃለል ማህበሩ በትጋት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የአምራችነት ቀን '' ከሸማችነት ወደ አምራችነት'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ በሚገኝበት በዛሬው ዕለት የመሰል ማህበራት ተሞክሮ የሚያስተምረው ነገር ብዙ ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም