በዓላትን ለማክበር የሚመጡ ጎብኚዎች ቆይታቸው የሰመረ እንዲሆን በቂ ዝግጅት ተደርጓል- ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች 

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፦ በዓላትን ለማክበር ከዓለም የተለያዩ ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቆይታቸው ያማረና የሰመረ እንዲሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች ሃላፊዎች ገለጹ። 

በኢትዮጵያም በየዓመቱ የሚከበሩ በዓላት የውጭ አገር ጎብኚዎች ቀልብን ከመሰባቸው ባሻገር ቁልፍ የቱሪዝም ገቢ አመንጪ ሁነቶች ናቸው።

2015 አሮጌ ተብሎ ለመሸኘት የቀናት እድሜ የቀረው ሲሆን የመስከረምን መጥባት ተከትሎ ዘመን መለወጫ፣ መስቀል፣ ኢሬቻና ጊፋታ በዓላት በተለያዩ ስነ- ስርዓቶች ይከበራሉ። 

የውጭ አገር ዜጎችም በዓላቱን ለመታደም ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።

መንግስት ለቱሪዝም ትኩረት በመስጠት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባቱ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ እያጎላው መጥቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች ሃላፊዎች አዲስ ዓመትን ተከትሎ የሚከበሩ በዓላትን ለመታደም የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ይላሉ።

የኤልገል ሆቴልና ስፓ ስራ አስኪያጅ አለማየሁ ፍቅረማርያም እንዳሉት ድርጅቱ የውጭ አገር ጎብኚዎች አለባበስና አመጋገብን ጨምሮ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት በሚያሳይ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል።

በአደባባይ በሚከበሩ በዓላት ላይም  የአገሪቱን  በጎ ገጽታ የሚያስተዋውቁ ስራዎች  ይዘው አንደሚቀርቡም  አመልክተዋል።

የቲኤች ቦንሮያል ሆቴል የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ኤደን ብዙነህ ሆቴሉ የተለያዩ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁ ሁነቶችን አዘጋጅቶ የቱሪስቶቹን መምጣት እየተጠባበቀ ይገኛል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ታሪኩ ኃይሉ በበኩላቸው በዓላቱን ለማክበር ሆቴሎች ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

የታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንትና አለም ትታይ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ዕንቁ ሙሉጌታና የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤንዲ አሰፋ በበኩላቸው ከበዓላቱ ጎን ለጎን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጎብኚዎች የተለያዩ የተፈጥሮ መስህቦችን እንዲጎበኙ የቱሪዝም ፓኬጆች መቀረጻቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑን ነው የተገለጸው።

በገበታ ለሸገርና በገበታ ለአገር መርሃ ግብር እንደ አንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርክ እንዲሁም ወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት አብዛኞቹ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከ280 በላይ ሆቴሎችና ከአንድ ሺህ በላይ በአገር አቀፍ ደረጃ አስጎብኚ ድርጅቶች እንዳሉ ከማህበራቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም