ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሮለታል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን በዘላቂነት እንዲደግፍ ተቋማዊ መዋቅር እንዲዘረጋለት መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ የአምራቹ ዘርፍ የአገሪቱ የዕድገት ምሰሶ ተብለው ከሚጠቀሱ መስኮች መካከል አንዱ ነው።

በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ መጀመሪያ ላይ 30 በመቶ ድርሻ የነበረውን የአምራች ዘርፍ የገበያ ድርሻ በዚህ ዓመት 34 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 37 በመቶ ማድረስ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

መንግስት ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ያሳድጋሉ ያላቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች እየወሰደ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሚያዚያ 29/2014 መጀመሩ ይታወቃል።

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን ዕድገትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንዲሁም አምራቾችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ያለመ ነው።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በንቅናቄው የአገር ውስጥ አምራቾች ምርታማነት ላይ ለውጦች መታየታቸውንና ባለሀብቶች በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎታቸው መጨመሩን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

በተለይም ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ከተነሱ ችግሮች መካከል የመሬት አቅርቦት ዋነኛው መሆኑንና በተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ለውጦች መታየታቸውን አመልክተዋል።

በንቅናቄው በፋይናንስ፣ በግብአት አቅርቦት፣ በወሰን ማስከበርና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ የመመለስ ተግባር በትኩረት መከናወኑን አመልክተዋል።

በዚህም ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ማምረት መመለሳቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።

ንቅናቄው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲያድግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትና ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠሩንም ነው ያመለከቱት።

በንቅናቄው የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስን በአገር ውስጥ በማምረት 60 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የተማሪዎች ዩኒፎርም በአገር ውስጥ እየተመረተ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።

የምግብ፣ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፎች በንቅናቄው የተሻለ ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ንቅናቄው ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖረው በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ወደ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትነት ማደጉን ጠቁመዋል።

በጽህፈት ቤቱ ግብርና፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማትና ግብአትን ጨምሮ በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ ክላስተሮች ተቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።

በዚህም ቀላል የማይባሉ አምራቾች በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ምርታማነትን እየጨመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕይወት አድን ምግቦችን በአገር ውስጥ እያመረተ የሚገኘው ሕሊና ገንቢ ምግቦች በማሳያነት ከሚጠቀሱ አምራቾች መካከል አንዱ ነው።  


 

እ.አ.አ በ1998 በለገጣፎ የተቋቋመው ሕሊና ገንቢ ምግቦች በኢትዮጵያውያንና በፈረንሳይ ባለሀብቶች የተቋቋመ የግል ኩባንያ ሲሆን በምግብ እጥረት ለተጎዱ ሕጻናት ማገገሚያነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ምግቦችን ያመርታል። 

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሕሊና በለጠ ድርጅቱ ሕይወት አድን ምግቦችን በአገር ውስጥ ማምረቱ ሕጻናት የምግብ እጦት ሲያጋጥማቸው ከውጭ ማስገባትን በማስቀረት ሕይወታቸውን መታደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።


 

በሌላ በኩል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምግብ እርዳታን በውጭ ምንዛሬ እየገዙ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚያደርጓቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ በማምረት ተቋማቱ ለግዢ የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ ከአገር ውስጥ እንዲገዙ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ለዜጎች የስራ ዕድልና ለአገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ነው ዋና ስራ አስኪያጇ የገለጹት።

በ2015 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ስራዎች ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የገቢ ምርቶች በአገር ውስጥ መተካታቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 የአምራችነት ቀን “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች መከበር ጀምሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም