አገርን በታማኝነት ማገልገል እና በጎነት የመከላከያ ሰራዊቱ መገለጫዎች ናቸው-የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት - ኢዜአ አማርኛ
አገርን በታማኝነት ማገልገል እና በጎነት የመከላከያ ሰራዊቱ መገለጫዎች ናቸው-የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ)፦ አገርን በታማኝነት ማገልገል እና በጎነት የመከላከያ ሰራዊቱ መገለጫዎች ናቸው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢፌዴሪ አየር ኃይል አባላት ተናገሩ።
ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ተከብሯል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢፌዴሪ አየር ኃይል አባላት የሀገር ክብርና የሉዓላዊነት መከታ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጎነት የዘወትር መገለጫው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሻለቃ ዮናስ ወልደማሪያም እንደተናገሩት የመከላከያ ሠራዊት ለአገር ህልውና ከሚከፍለው መስዋዕትነት በተጨማሪ ህዝብን በበጎነት የሚያገለግል የኢትዮጵያ መከታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአገር ፍቅርና በጎነት የሠራዊቱ መገለጫ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሻለቃ ኢብራሂም ኑሩ በበኩላቸው የአገር መከላከያ ሰራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት መካከል ከራስ በፊት ለህዝብና ለአገር የሚለው ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት ለአገሩም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም መከበር መሰዋትነት የሚከፍል ምስጉን ሰራዊት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሰራዊቱ ካለው ላይ ቀንሶ ወገኖቹን በማገዝ የበጎነት ተምሳሌት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ውድ ህይወቱን ለሀገር ሉዓላዊነት በፈቃዱ ለሚሰጠው የመከላከያ ሰራዊት የበጎነት ቀን ልዩ ትርጉም እንዳለው የተናገሩት ደግሞ ኮሎኔል ደረጄ አስታጥቄ ናቸው።
የአገር ሉዓላዊነት፡ ልማትና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሠራዊቱ የህይወት መስዋእትነትና በጎነት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮ ዓመት የጳጉሜን ወር ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች የተሰጣቸው ሲሆን፤ በነገው እለት ጳጉሜን 4 የአምራችነት ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል፡፡