ቀጥታ፡

በአፍሪካ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ) ፦ በአፍሪካ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን በአፍሪካ ሰላምና ልማትን ማስቀጠል የሚያስችል ቀጣናዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩም ግጭትና የሰላም እጦት በተለይ ታዳጊ የአፍሪካ አገራትን ኢኮኖሚ በብርቱ እንደሚጎዳ ተመላክቷል፡፡

በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚከሰት ግጭት የሀገራቱን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት እስከ 8 በመቶ እንደሚቀንስ የዓለም ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም በአፍሪካ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ማስፋፈያ ፕሮጀክቶች ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን ካላረጋገጡ በአህጉሪቱ እስከ 2030 ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ሥራ አጥ ዜጎች ይፈጠራሉ ብሏል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ መድረክ እንዳሉት፤ ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ግጭትና ድህነትን ማስወገድ ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ ሀገራት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በተሟላ ሁኔታ ማስከበር አለባቸው ብለዋል፡፡

"ልማት ኢኮኖሚያዊ እድገት ብቻ አይደለም" ያሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ልማት የተሟላ የሚሆነው ማህበረሰቡን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ማድረግ ሲችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰላም፣ ልማትና ሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በእነዚህ ሶስቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችል የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ማዘጋጀቷን ገልጸው፤ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፤ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠርና የህግ የበላይነትን ማስፈን የዕቅዱ ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ሰላምና ዘላቂ ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስና በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበይነ መረብ አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ያለ ዘላቂ ሰላም የሰብዓዊ መብት በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ መብቶችን ያለ ገደብ ለማክበር ሀገራት ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶችን መገንባትና ፍተሃዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የማህበራዊ ፖሊሲ ኃላፊ ሳውራብህ ሲንሃ በበኩላቸው፤ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2050 በዓለም ላይ ካሉ ሶስት ወጣቶች አንዱ አፍሪካዊ እንደሆነ ገልጸው፤ ከ20 እስከ 36 ዓመት ያሉ መስራት የሚችሉ ወጣቶች ቁጥር አሁን ካለበት በሁለት እጥፍ ያድጋል ብለዋል፡፡

በዚህም አፍሪካውያን ሥራ ፈላጊዎች ቁጥር የዓለምን 25 በመቶ እንደሚሸፍኑ ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ያሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ገቢራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም