ቀጥታ፡

የተደረገልን በጎና መልካም ተግባር በቀጣይ ህይወታችንን ለመለወጥ የሚያግዘንና ተስፋ የሰጠን ነው -በድሬዳዋ የበጎ ተግባር ተጠቃሚዎች

ድሬዳዋ፣ ጳግሜን 3/2015 (ኢዜአ) -የተደረገላቸው በጎና መልካም ተግባር ያሉባቸውን መሠረታዊ ችግሮች የሚያቃልሉ፣ ለቀጣይ ህይወታቸው መለወጥ የሚያግዟቸውና ተስፋ የሰጧቸው መሆኑን የድሬዳዋ የበጎነት ተግባር  ተጠቃሚዎች ገለጹ።

ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን "በጎነት ለአገር"  በሚል  መሪ ሃሳብ ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል።

በቀኑ አከባበር ስነ ስርአት ላይ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች ለችግረኛ ተማሪዎች በድጋፍ ተበርክተዋል።

ድጋፉን ያደረጉት የፌደራል ቤቶች  ኮርፖሬሽን  የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከትና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው።

ድጋፉ ደብተሮች፣ እስክሪቢቶ፣ ቦርሳዎችና የትምህርት ቤት የደንብ  ልብሶችን ያካተተ ሲሆን  ከ600 በላይ  ለሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎች ተበርክቷል ።

በተጨማሪም የፌደራል ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ  ለሁለት ችግረኛ ቤተሰቦች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረክቧል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የ5ተኛ ክፍል ተማሪ ናርዶስ ሳምሶን “የተሰጠኝ የመማሪያ ቁሳቁስ  ትምህርቴን ያለምንም መሳቀቅ እንድከታተልና የተሻለ ውጤት እንዳመጣ  ያግዘኛል”  ብላለች።

በትምህርቷ ውጤታማ በመሆን ወደፊት ህይወቷን በተሻለ መንገድ ለመምራት በሚያስችላት መስክ ለመሰማራት መነሳሳት የፈጠረባት መሆኑን ገልጻለች።

በድሬዳዋ ከዚራ ቤት ተገንብቶ ከተሰጣቸው ቤተሰቦች መካከል አቶ ሙስጠፋ ጠሐ በበኩላቸው የተደረገኝ በጎና መልካም ስራ መጪውን ህይወቴን ያለመለመና ትልቅ ተስፋ የሰጠኝ ነው” ብለዋል

"ይህን በጎ ስራና ተግባር እጅ ለእጅ በመያያዝ አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ የኔን መሰል ችግረኛ ቤተሰቦች ህይወት መለወጥ ይቻላል ብዬ አምናለሁ" ሲሉም አክለዋል።

ነዋሪዎቹ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

ድጋፉን ያበረከቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በወቅቱ እንዳሉት ይህ የመደጋገፍና የመረዳዳት የድሬዳዋ እሴት በአዲሱ አመት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ።

በድሬዳዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል የተጀመሩ በጎ ስራዎች  በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው  አስገንዝበዋል።

ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም