በበጎ ሥራቸው በርካታ አካል ጉዳተኞችን ከችግራቸው እየታደጉ ያሉት የጅግጅጋዋ እናት 

ጅግጅጋ ፣ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ)   በበጎ ሥራቸው በርካታ አካል ጉዳተኞችን ከችግራቸው እየ

ወይዘሮ ሲመን ሙሁመድ ይባላሉ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ከንግድ ሥራቸው በተጨማሪ በበጎ ተግባራትን ያከናውናሉ።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሌሎችን በማስተባበር በሚያከናውኑት በጎ ተግባር በከተማዋ አካል ጉዳተኞችን፣ ችግረኛ ተማሪዎች፣ እናቶች እና አዛውንቶችን እየደገፉ ይገኛሉ።  

የበተለይ በከተማዋ የአካል ጉዳት ላጋጠማቸው ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ ይታወቃሉ ወይዘሮ ሲመን።

ግለሰቧ ለኢዜአ እንደገለጹት በአካል ጉዳታቸው ምክንያት ለመንቀሳቀስ የተቸገሩና በሰው እገዛ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወገኖች ባለሦስት እግር የተሽከርካሪ ድጋፍ በማግኘታቸው ከቤት መውጣትና መስራት ችለዋል።

አካል ጉዳተኛ የሆኑ ህጻናት ተማሪዎች፣ እናቶችና አዛውንቶች በተደረገላቸው የተሽከርካሪ ድጋፍ በነጻነት ሲንቀሳቁ ሳይ ብርታት ይሆነኛል ሲሉም ተናግረዋል። 

ብዙ አካል ጉዳተኞች ችግራቸው ተፈቶ ለዓመታት ከተደበቁበት ወጥተዋል ያሉት ወይዘሮ ሲመን፣ በጎ መስራት ጥቅሙ ለራስ በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የበጎ ስራውን ከጀመሩ አምስት ዓመታት ማስቆጠራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሲመን፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከርና ሥራውንም ተቋማዊ ለማድረግ "ሲመን ፋውዴሽን" የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ነው።  

የተጎዱና የጤና እክል የገጠማቸውን ወገኖችን ከማሳከም ባለፈ አካል ጉዳተኞች ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ተጠቃሚ አድርገዋል።  

እስካሁንም የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ለ36 አካል ጉዳተኞች የመንቀሳቀሻ ተሽከርካሪ በድጋፍ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከእዚህ በረጨማሪ በራሳቸው ከፍለው መታከም ላልቻሉ ከ250 በላይ ህሙማን የሕክምና ወጪያቸውን ሸፍነው በጅግጅጋና በአዲስ አበባ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች እንዲታከሙ አድርገዋል።

ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ድጋፍ ከተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች መካከል አቶ አደን ኡመር ከልጅነታቸው ጀምሮ የመንቀሳቀስ ችግር እንደነበረባቸው ገልጸዋል።

በእዚህ ምክንያት በነጻነት ለመንቀሳቀስም ሆነ ከህብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል ተቸግረው እንደነበር አስታውሰው፣ ተሽከርካሪውን ካገኙ በኋላ በቀላሉ መንቀሳቀስ እንደቻሉ ተናግረዋል። 

ቀዳም ሲል በህብረተቡ ውስጥ አካል ጉዳተኝነት የፈጣሪ ቁጣና የእርግማን ውጤት ተደርጎ ስለሚታሰብ ለዓመታት ቤት ውስጥ ተደብቀው እንደኖሩ ያስታወሱት አቶ አደን፣ ዛሬ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ላገዟቸው በጎ አድራጊ ግለሰብ አመስግነዋል።

በወይዘሮ ሲመን ድጋፍ ልጃቸው ውጭ ሀገር ድረስ ሄዶ የህክምና አገልግሎት ማግኘቱን የገለጹት ደግሞ አቶ አብዲ አብዱላሂ የተባሉ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

አቶ አብዲ እንዳሉት ከአራት ዓመታት በፊት በቤታቸው በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ልጃቸው ተጎድቶ ለዓመታት ምግብ መብላትም ሆነ ምራቁን መቆጣጠር ተስኖት ነበር።  

 

በወቅቱ በሀገር ውስጥ ህክምና መፍትሄ እንደማይገኝ ቢነገራቸውም ከሀገር ውጪ ወስዶ ለማሳከም የገንዘብ አቅም ፈተና እንደነበረባቸው አስታውሰዋል። 

 

"የልጄን ህመምና ስቃይ በየቀኑ መስማት ከባድ ነበር" ያሉት አቶ አብዲ፣ "የግለሰቧን በጎ ተግባር ስራ ሰምቼ ልጄን እንድታሳከምልኝ ጠይቋት" ይላሉ።

 

ወይዘሮ ሲመን ከተለያዩ አካላት አሰባስበው ባደረጉላቸው ከ21ሺህ ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ልጃቸው ወደ ህንድ ሀገር ሄዶ ለመታከም መቻሉን ተናግረዋል። 

 

በአሁኑ ወቅትም ልጃቸው ቀና ብሎ መራመድ፣ ያለችግር መብላትና ምራቁንም መቆጣጠር በመቻሉ ደስተኛ መሆናቸውን ነው አቶ አብዲ የተናገሩት። 

 

የሶማሌ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካል ጉዳተኞች ልማት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፣ ግለሰቧ በበጎ ፍቃድ ተነሳስተው ልዩ ፍላጎት ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ ጠንክረው በመስራት የበርካታ ወገኖችን ችግር እያቃለሉ እናት መሆናቸውንም ነው የገለጹት።  

አቶ መሀመድ እንዳሉት በግለሰቧ አስተባባሪነት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ድጋፍ ያገኙ አካል ጉዳተኞች  የተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ገቢ ማግኘት ጀመረዋል። 

 

 

 

 

 

ታደጉ ያሉት የጅግጅጋዋ እናት 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም