“በጎነት ህይወት ነው፤ ለሰው መኖርን ብቻ ነው የሚጠይቀው" - ወጣት ተስፋ አለባቸው

 

ሐረር የአገር ልጅ የበጎ አድራጎት ማህበር በ2008 ዓ.ም በጎዳና ላይ የነበሩ 40 ልጆችን ከጎዳና ህይወት አንስቶ በመንከባከብ ነው ሥራውን የጀመረው።

የማህበሩ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ተስፋ አለባቸው እንደገለጸው፣ በአሁኑ ወቅት ማህበሩ 166 ህጻናትን ተንከባክቦ እያስተማረና እያሳደገ ይገኛል።

በጎነት "ህይወት ነው፤ መኖርን ብቻ ነው የሚጠይቀው” የሚለው ይህ ወጣት፣ "እየኖሩ ይህን ማድረግ ደግሞ መንፈስን ያድሳል፤ ህይወትም ይሰጣል" ይላል።

"ለእኔ ፈጣሪ ካሟላልኝ እኔ ደግሞ ለሌሎች ማድረግ አለብኝ" የሚለው ወጣት ተስፋ፣ ማንኛውም ሰው ከራሱ ባለፈ ለሌላው የሚችለውን ማድረግ እንዳለበት ነው የገለጸው።

ወጣት ተስፋ እንዳለው ማህበሩ በስምንት ዓመት የበጎ አድራጎት ሥራው ተንከባክቦ ያሳደጋቸውን ልጆች ለቁም ነገርም አብቅቷል።

በክለብ ደረጃ አንድ የእግር ኳስ ተጫዋች እና ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃንን ያፈራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ልጆች መኖራቸውን ተናግሯል።


ከዚህ በተጨማሪ ማህበሩ 208 ህጻናትን ከወላጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በማገናኘት ህጻናቱ የተስተካከለ ህይወት እንዲኖሩ ማድረጉን ነው የገለጸው።

ማህበሩ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ካሉ በጎ ፍቃደኞች ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የጠቀሰው ወጣት ተስፋ፣ በዚህም ለህጻናቱ የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት እየተንከባከበ መሆኑን ተናግሯል።

ማህበሩ እያከናወናቸው ባሉ በጎ ተግባራት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከክልሉ ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት በቅርቡ ድጋፍ ማግኘቱንም ነው ወጣቱ የገለጸው።

ማህበሩ በቅርቡ በከፈተው ሁለተኛ ቅርንጫፉም ታዳጊ ህጻናትን ከሱስ ነጻ በማድረግ መልሶ ከቤተሰብ ጋር የማገናኘት ሥራም እያከናወነ ይገኛል።

"ህጻናትን ለመታደግ በማከናውነው ሥራ ደስተኛ ብሆንም የሰራሁት ስራ የሚያኩራራ አይደለም" የሚለው ወጣት ተስፋ፣ በቀጣይ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ልጆች ሥራ መያዝ እንዲችሉ የሞያ ማሰልጠኛ ተቋም ለመክፈት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግሯል።


ወደ ተቋሙ ከመጣሁ ስድስት ዓመት ሆኖኛል ያለው ወጣት ሃምዲ አልይ በበኩሉ፣ በአሁኑ ወቅት 12ኛ ክፍል መድረሱንና ለቤተሰቦቹም ተስፋን ሰንቆ እየተማረ መሆኑን ነው የገለጸው።

"በጎነት በፈጣሪም የሚያስመሰግን ተግባር በመሆኑ ተስፋ የጀመረውን የበጎ አድራጎት ስራ ሳድግ ለማስቀጠል ራዕይ ይዤ ተነስቻለሁ" ብሏል።

ወደማህበሩ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ደስተኛ ህይወት እየመሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ተማሪ አይሻ አብዱላሂ እና ሳሙኤል እስራኤል ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የ8ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች የገለጸችው ተማሪ አይሻ ወደማህበሩ ከመጣች በኋላ የደረጃ ተማሪ መሆኗን ተናግራለች።

መልካምነት መልሶ ለራስ የሚደርስ ተግባር በመሆኑ ወደፊት በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለመሰማራት መነሳሳቷን ጠቁማለች።

በበጎ አድራጎት ሲኖር ደስተኛ መሆኑን የተናገረው ህጻን ሳሙኤል እስራኤል በበኩሉ የምፈልገውን ነገር ከማህበሩ እያገኘሁ ነው ብሏል።

በቀጣይ ውጤታማ ተማሪ ሆኖ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ትምህርቱን በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል።


ከአንድ ወር በፊት ለሐረር የአገር ልጅ የበጎ አድራጎት ማህበር የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በወቅቱ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ ሥራ በራስ ጥረት ተነሳስቶ ሌላውን የማገዝ ተግባር ነው።

በጎነት ለሰው ልጅ ህይወት መራራትና ማሰብ በመሆኑ እንደ ሐረር የአገር ልጅ በጎ አድራጎት ያሉ ማህበራት ሊጠናከሩ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም