ቀጥታ፡

በጎነት ሁሉንም ያለልዩነት የምናገለግልበት ተግባር በመሆኑ ሁሌም እራስን ለበጎ ሥራ ማዘጋጀት ይገባል -- አቶ ኦርዲን በድሪ 

ሐረር፣ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ)፡- በጎነት ሁሉንም ያለልዩነት በቀናነት የምናገለግልበት ተግባር በመሆኑ ሁሌም እራስን ለበጎ ሥራ ማዘጋጀት ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ጳጉሜን 3- የበጎነት ቀን በማስመልከት በሐረር ከተማ ለአረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ ለተማሪዎች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአቅመ ደካሞች የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። 

በድጋፍ መርሀግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት፣ በጎነት ሁሉም  አቅሙ በፈቀደ መጠን የሚሳተፉበት ተግባር ነው።

"ብሔር፣ ሃይማኖት እና ቀለም ሳይለይ ሁሉንም ሰው በቀናነት የምናገለግልበት ተግባር በመሆኑ ሁሌም እራስን ለመልካም ስራ ማዘጋጀት ይገባል" ብለዋል።

“በጎነት ለራስ ነው፤ በጎነት ለአገር ነው።” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በበጎነት የሚገኘው ውስጣዊ እርካታ ለራስ መሆኑን አስረድተዋል።

"መልካም ሥራ ባልታሰበ ወቅት የሚከፍል በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።  

ወገንን ለማገልገል የሚፈጸም በጎ ተግባር በወሰን የማይገደብና የሕሊና እርካታ የሚሰጥ ተግባር በመሆኑ ዓመት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሊፈጸም የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

"በጎነት ለሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ  በተከበረው የበጎነት ቀን “መስጠት መቀበል” መሆኑን የሚያስገነዝቡ የተለያዩ ሁነቶች ተከናውነዋል።

አቶ ጌቱ እንዳሉት ከበጎ አድራጊ ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ከሐረር ወዳጆች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፎች ተደርጓል።

ዛሬ በበጎነት ቀን ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተደረጉ ድጋፎች መካከል የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና ቦርሳ፣ ለአካል ጉዳተኞች መንቀሳቀሻ ዊልቸር እና ክራንች እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

ቀኑን በማስመልከት በክልሉ በሚገኘው የአብርሃ ባህታ አረጋውያን መርጃ ተቋም የሚገኙ አረጋዊያንን በመጎብኘት የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ ለአካል ጉዳተኞች የዊልቸርና ክራንች ድጋፎችን ጨምሮ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ስራም አመራሩ አስጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላምን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም