ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰጥ የደም ልገሳ ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባል-የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ) ፡- በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰጥ የደም ልገሳ ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ የሚባለው የደም ልገሳ በፍጹም ፍላጎት እና ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን በጎ ተግባር ነዉ፡፡

ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ በቆየው የደም ልገሳ አቅርቦት ስርዓት ውስጥ፤ በየአመቱ የደም ፍላጎት በ 10 በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የብሔራዊ ደም ባንክ አስታውቋል፡፡

በተለይም የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሕይወትን፣ እንዲሁም የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎችን እና በጽኑ ህመም ላይ ለሚገኙ ታካሚዎችን ሕይወት የሚቀጥለው ደም ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጳጉሜን 3 'በጎነት ለሀገር' በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የበጎነት ቀን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ አነጋግሯል።

አቶ ሀብታሙታዬ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በበጎ ፍቃድ ደም የሚለግሱ ዜጎች ቁጥር መሻሻል ቢያሳይም ከሚፈለገው ደም አንጻር በቂ አይደለም፡፡

በዘንድሮ አመት ከበጎ ፍቃደኞች 352 ሺህ 996 ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸው በ2014 ከተሰበሰበው የ15 ሺህ ዩኒት ደም ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም 85 በመቶ የደም ፍላጎትን መመለሰ ያስቻለ ሲሆን በተለይ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰጥ የደም ልገሳ ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አክለዋል።

በአዲሱ ዓመት የደም ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ በማሳካት በደም ማጣት የሚያልፍን ውድ ህይወት ለመታደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ መደበኛ ደም ለጋሾች 2 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንኑ ቁጥር ወደ 10 በመቶ በማሳደግ አስተማማኝ የደም አቅርቦት እንዲኖረን ህብረተሰቡ በአዲስ ዓመት ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል፡፡

የደም ባንኩ በመጪው አዲስ አመት ከበጎ ፈቃደኞች 500 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ የደም ስጦታ የህይወት ስጦታ መሆኑን በመረዳት በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ ባህል በመደበኛነት እንዲያዳብር ጥሪ አድርጓል።

ደም የማይሸጥና የማይለወጥ ከበጎ ፈቃደኞች ተሰብስቦ ህክምና ለሚሰጡ ጤና ተቋማት በነፃ የሚቀርብ በመሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በሰፊው ያስፈልጋል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የደም ባንክ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በመገኘት በቋሚነት ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአዲሱ አመት በሶስት ወር አንድ ጊዜ በቋሚነት ደም በመለገስ ህብረተሰቡ ሰብአዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም