መጪውን አዲስ አመት ታሳቢ በማድረግ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለተጠቃሚ ማቅረቡን - የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
መጪውን አዲስ አመት ታሳቢ በማድረግ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለተጠቃሚ ማቅረቡን - የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2015(ኢዜአ)፦ መጪውን አዲስ አመት ታሳቢ በማድረግ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት ከውጭ በማስገባት ለተጠቃሚ ማቅረቡን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ።
ድርጅቱ ለበዓል የሚሆኑ ዘይት ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ለቆዳ ማልፊያ የሚሆን የኢንዱስትሪ ጨው እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀቱን ገልጿል ።
የድርጅቱ የግዢ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ግርሻ ለኢዜአ እንደገለጹት ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉ 83 ቅርንጫፎች ለህብረተሰቡ የተለያዩ ምርቶችን በማከፋፈል ገበያን የማረጋጋት ተግባር ሲሰራ ቆይቷል።
አዲሱን አመት ታሳቢ በማድረግ ለበዓሉ የሚሆን 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለህብረተሰቡ ማከፋፈል መጀመሩን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለተጠቃሚው መቅረቡን ገልፀው፤ ቀሪው ደግሞ እስከ መስቀል በዓል መዳረሻ ለህብረተሰቡ እንደሚቀርብ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለበዓሉ የሚሆን በቂ የዳቦ ዱቄት አቅርቦት እንዳለና ከ 5 ኪሎ ጀምሮ ባሉ የተለያዩ አማራጮች ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለበዓሉ የሚታረዱ እንስሳት ቆዳን ለማልፋት የሚሆን የኢንዱስትሪ ጨው በበቂ ሁኔታ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል።
ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የሚሆን ደብተር በድርጅቱ አርማ ታትሞ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማከፋፈል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።