"በጎ ፈቃደኝነት በህይወት ዘመኔ የምከውነው የነብሴ ጥሪ ነው" - ኢዜአ አማርኛ
"በጎ ፈቃደኝነት በህይወት ዘመኔ የምከውነው የነብሴ ጥሪ ነው"
በጎነትን ለሩብ ምዕተ ዓመት የከወነው ጎልማሳ ብሩክ ወርቁ ትውልድና ዕድገቱ መሃል አዲስ አበባ፣ ወይራ ሰፈር አካባቢ ነው።
"በጎነት የሰውነት ትርጉም የሚፈታበት ተግባር ነው" የሚለው ብሩክ፣ በበጎነት አገልግሎት 25 ዓመታት አሳልፏል።
'በጎነት ይከፍላል' እንዲሉ፣ ብሩክ የበጎነት እሴትን የባህሪ ገንዘቡ ያደረገው ከራሱ የልጅነት ልምምድ ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ በጎ ሰዎች በዋሉለት ውለታም መነሻነት ጭምር ነበር።
በ27 ዓመት ዕድሜው በድንገት የቲቢ በሽታ ያጋጠመው ብሩክ፤ ከህመሙ ለመፈወስ ኢኮኖሚያዊ አቅም ቢያጥረውም በተወሰኑ ወጣቶች አስተባባሪነትና በበጎ ሰዎች ትብብር ገንዘብ ተዋጥቶለት ከሞት ተርፏል።
"የሰው መድኃኒቱ ሰው ነው" የሚለው ብሩክ ሕይወቱን በታደጉት የትውልድ ሰፈሩ ወጣቶችና ዕጁን ለዘረጋለት ማህበረሰብ ውለታን ለመመለስ በጎነትን በተግባር ለመኖር መወሰኑን ይናገራል።
በዚህም ላለፉት 25 ዓመታት ቃልና ተግባርን አጣምሮ እና ሌሎች ወጣቶችን አስተባብሮ ባለው አቅም ሰዎችን በበጎነት ሲያገለግል ቆይቷል።
እግረኞ ማቋረጫዎች ሰዎችን ያሻግራል፣ በአዘቦትም ሆነ በበዓላት ወቅት የፍጆታ ዕቃዎች አሰባስቦ ለአቅመ ደካሞች በመስጠት ለበርካቶች ተስፋና ኃይል ሆኗል።
ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር መስራች መካከል የሆነው ብሩክ፣ በ1993 ዓ.ም ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር እንጦጦ አካባቢ የተራቆተ አካባቢን ችግኝ በመትከል የራሱን አሻራ አኑሯል።
በጎነት ከመልካም ዕሳቤ የሚመነጭ እንጂ በገንዘብና በዕውቀት እንደማይገደብ ገልጾ፤ ሕብረተሰቡን ሳገለግል የነፍሴ ጥሪ የሆነውን ፅዋዬን እንደተጎነጨው ይሰማኛል ይላል።
በጎ ፈቃድ ግለሰቦችን ከመርዳት በላይ ሀገር ግንባታ አካል እንደሆነ ገልጾ፤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር ወጣቶች የበጎነት እሴት እንዲወርሱ እየሰራ መሆኑንም ይናገራል።
በጎ ፈቃደኝነት በህይወት ዘመኔ የምከውነው የነብሴ ጥሪ ነው የሚለው ብሩክ፤ በጎነት ወደፊት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልጻል።
በጎነት በመስጠት ውስጥ ያለ በእውነትኛ ስሜት ሌሎችን ባለ አቅም እና ጉልበት የሚረዳበት የሰውነት ትርጉም የሚፈታበት ተግባር ነው ሲልም አክሏል።
ከ10 ዓመታት በላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልምድ ያላት ወጣት ረሂማ ዋበላ በበኩሏ "በጎነት መሰጠት ይጠይቃል" ትላለች።
በትውልድ ሰፈሯ አንድ የአብሮ አደግ ማህበር በማቋቋም ሌሎች በገንዘብ እና በጉልበት እንዲረዱ ጥረት አድርጋለች።
በአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ስር በመሆን ለዓመታት በምትሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሌሎች ደስታ፣ የራሷን ደስታ እንዳገኘች ገልጻ፤ እገዛ ከሚሹ ወገኖች ጋር በአብሮነት በመስራቷ ትደሰታለች።
በጎ ፈቃድ ብዙ ያልተሰራበት ግን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉበት እሴት በመሆኑ ሁሉም ሰው ሊላበሰው እንደሚገባ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ በጎ ፈቃደኞቹ ይናገራሉ።