በጎነት ለሌሎች መኖር ነው- ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ 

 

"በጎነት ለሌሎች መኖር ነው" ሲሉ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ተናገሩ። 

በኢትዮጵያ የጳጉሜን ቀናት የተለያየ ስያሜ በመስጠት በጎነትን ፣አብሮነትን ፣መተሳሰብንና መስዋዕትነትን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን በመስጠት መከበር ከጀመረ ቆይቷል።

በዚህም የዛሬዋ ጳጉሜን 3 ቀን “በጎነት ለሀገር” በሚል ሀሳብ በጎ ተግባራትን በሚያንጸባርቁ የተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው። 

ቀኑን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደርን አነጋግሯል።

"የኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን" የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

ከተመሰረተ 29ኛ ዓመቱን የያዘው ድርጅቱ ከ11 ሺህ ያላነሱ ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋዊያንን በመንከባከብና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ከ39 ሺህ በላይ ሕፃናትን ደግፎና አስተምሮ ለቁምነገር ማብቃት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ላለፉት 17 ዓመታት "ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን" በሚል መርህ በሀገር ልጆች ሀብት ላይ ተመስርቶ በሶስት ክልሎች በ 24 ከተሞችና 112 ወረዳዎች ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በትምህርት፣ጤና፣ የሕጻናት ጥበቃና የኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበትና አረጋውያንን የመንከባከብ  ስራዎችን በስፋት ሲያከናወን መቆየቱን ይጠቀሳሉ። 

በጎነት ለሌሎች መኖር ነው የሚሉት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፤ በጎነት ሕይወትንና ስኬትን ሙሉ የሚያደርግ እሳቤ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጎነት ለግለሰብም ሆነ ለማህበረሰብ ብሎም ለአገር የሚጠቅም በጎ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

በጎነት ለሁሉም ሰው የተሰጠ ነው የሚሉት  ሲስተር ዘቢደር ልዩነቱ በጎነትን መለማመድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን በመተባበር ለአገርና ለወገን ትልቅ ስራ ማከናወን ይቻላሉ ብለዋል። 

በመስጠት ብዙ መቀበል እንደሚቻልና በጎነት የሕይወት አካል ማድረግ እንደሚገባም ነው ሲስተር ዘቢደር የገለጹት።

ሜሪጆይ በ1986 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በተቀናጀ የልማት መርሐ-ግብሮች ለችግር የተጋለጡና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ዋና ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም