ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና አስተማማኝ አየር ኃይል የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና አስተማማኝ አየር ኃይል የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በተቋሙ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉና የላቀ አፈጻጻም ላሳዩ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል።

የአየር ኃይል ለከፍተኛ መኮንኖችና አመራሮች የሜዳሊያ፣ ሪቫንና የምስክር ወረቀት የመስጠት መርሐ-ግብር አካሄዷል።

በዚሁ መሰረት ተቋሙን ከ25 እስከ 35 ዓመት ላገለገሉ አምስት ከፍተኛ መኮንኖች በየደረጃው የውትድርና አገልግሎት ሜዳሊያና ሪቫን እንዲሁም ሰርተፊኬት  ሸልሟቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ እንዲሁም በሰራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ የማዕረግ አመላመል ስርዓትን መሰረት በማድረግ መስፈርቱን ያሟሉ 585 መኮንኖች የማዕረግ እድገት ተሰጥቷቸዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ተቋሙ በሰው ኃይልና ተቋም ግንባታ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ወታደራዊ አቅምን የማጎልበት እንዲሁም በአስተሳሰብና በሙያ የሰው ኃይሉን ማብቃት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ዘመናዊና አስተማማኝ አየር ኃይል የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እኛ እያለን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ማንም ሊደፍራት አይችልም ያሉት ጄኔራሉ በመጪው ዓመት በተሻለ ግዳጅ አፈጻጸም ተቋማዊ ስኬት ለማምጣት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው የሰራዊቱ አባላት ኢትዮጵያን በላቀ ትጋት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የማዕረግ እድገት ያገኙ የሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው የተሰጠን የማዕረግ እድገት ለቀጣይ ግዳጅ አፈጻጸም ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የአየር ኃይል የበጎነት ቀንንና የዘመን መለዋጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በቅጥር ግቢው ያመረተውንና ተፈጭቶ የተሰናዳውን የስንዴ ዱቄት ከቢሾፍቱና አካባቢው ለተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች አበርክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም